Wednesday, November 25, 2009

ኸረ ለመሆኑ ቦርድ ማድረግ የቻለው ነገር ምንድነው?

የአስተዳደር ቦርዱ እንደ ቦይ ውሃ ማንም ሲነዳው ባይነዳ ፤ እራሱን ችሎ በማስተዋል እያሰበ ቢሠራ፤ አባላቱን ሁሉ በእኩልነት የሚመለከትበት ያልተጠናገረ ጤናማ ዓይን ቢኖረው፤ማኅበረ ቅዱሳንን ከቤተክርስቲያን አጠፋለሁ ብሎ ባይነሣ፤እልኸኛ ባይሆን፤እንዲያገለግል የተመረጠው ቤክርስቲያንን እንጂ ቀበሌን አለመሆኑን ቢያውቅ ኖሮ፤ተው ሲሉት የነበሩትን አማካሪ ሽማግሌዎቹን ቢሰማ ኖሮ ፤ ውሸታም ሆኖ በፍርድ ቤት ፊት ሳይቀር ባይወሻክት ኖሮ ወ.ዘ.ተ.. እዚህ ሁሉ ማጥና ቅሌት ውስጥ አይወድቅም ነበር፡
ሕግ የተሠራው ሕግን የማያከብሩ ሁሉ እንዲቀጡበት ነው፡፡ ሕግ የበላይ ነውና የግድ መከበር አለበት ፡፡ በተለይም ይህ የምንኖርበት ሃገር የሠው ልጆች ነጻነትና የእኩልነት መብት የተረጋገጠበት ሀገር ስለሆነ ሥርዓተ አልበኝነትና ዋልጌነት ቦታ የላቸውም፡፡ለዚህ ነው የደብራችን ቦርድ ሲነገረው አልሠማ ብሎ ራሱን አዋርዶ ቤተክርስቲያናችንንም እያዋረደ ያለው፡፡

የሚገርመው ነገር ቦርዱ እንዲህ ችግርና መካራ ውስጥ ወድቆ እያለ በእርሱ እግር ተተክተው የእርሱን ቅሌት እንደገና ለመልበስ በምርጫ ሰበብ ለመግባት ያሰፈሰፉ በወላጅ ኮሚቴ ውስጥ ያሉት የወገኖቻችን ነገር ነው፡፡ ሁሉም ሠው ማወቅ ያለበት ነገር ቢኖር ሥልጣን መልካም ነገር ሲሠሩበት እንጂ ሲባልጉበት አዋራጅ መሆኑን ነው፡፡ እነርሱም ከደጅ ሆነው ለመግባት ሲፎክሩ የነበረው ቦርድ በአቅም እጦት ሳያጠፋ የቀረውን ጥፋት እነሱ በአዲስ ኃይል እንደ ገና ተጠናክረው ለማጥፋት ነበር ፡፡

ለምሳሌ እጩዎቹ ቦርድ ሆነው ቢመረጡ ኖሮ የመጀመሪያ ሥራቸው አድርገው አቅደውት የነበረው ሁለቱን ካህናት በድምጽ ብልጫ አይለው ከሥራቸው ለማሰናበት ነበር፡፡ መሪዎቻቸው የሆኑት ሂሳብ ሹምና ገንዘብ ያዡ ሥራዎቻቸውን ትተው ቀንና ሌት ያስቡ የነበረው እነዚሁኑን ካህናት እንዴት እናባር እያሉ ነበር፡፡ ‹እስቲ የተመኩበት መስቀል ሲያድናቸው እናያለን› እያሉ በድፍረት እስከመናገርም ደርሠው ነበር፡፡ ይህ አባባል ግን በእውነት ትልቅ የሃይማኖት ጉድለት ያለበት ነው፡፡ የመስቀሉ ቃል ለማያምኑት ሞኝነት ለሚያምኑት ደግሞ የመዳን ኃይል ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ሚያምን ሁሉ ይድናል ከክፉ ነገርም ይጠበቃል ፡፡ ይህ በቦርድና በሁሉም አማኞች ዘንድ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ቦርድ ለጥፋት ሥራዬ አልተመቹኝም ያላቸውን ማኅበረ ቅዱሳንን አባርራለሁ ብሎ ተነሣ፡፡ አልቻለም፡፡ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አዲስ የሸሪያ ሕግ አውጥቶ በዚህ እያስፈራራሁ አስተዳድራለሁ አለ፡፡ አልቻለም ፡፡ ከጥፋት ሥራዬ ጋር አልተባበሩኝምና ሁለቱን መምህራን ካህናት አባርራለሁ ብሎ ተነሣ ፡፡ አልቻለም፡፡ በሠላሳ ብር የአባልነት ግዴታ ክፍያና በሦስት መቶ ብር የክርስትና ክፍያ የቤተ ክርስቲያኗን ካዝና ሞላለሁ ብሎ ቋምጦ ተነሣ ፡፡አልቻለም ፡፡ እንዲያውም ለፖሊስ እንጂ ለቢልና ለሠራተኞች ደሞዝ የሚከፈል የለም እያለ እያወጀ ነው፡፡ሌሎቹን አባላት ያገለለ ቡድናዊ ምርጫ አደርጋለው ብሎ ተነሣ ፡፡አልቻለም፡፡ ያወጣውን የሸሪያ ሕግ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እንዳይቀበሉት የሚያስተባብሩ ከሳሾችን ከቤተ ክርስቲያን በፖሊስ ለማስወጣት ሞከረ፡፡ ግን አልቻለም፡፡ ኸረ ለመሆኑ ቦርድ ማድረግ የቻለው ነገር ምንድነው ? ምንም ፡፡

ቦርድ መልካሙን ነገር ይቅርና ታጥቆ የቆመለትን የክፋት ሥራ እንኳን ተሳክቶለት ሊሠራው አልቻለም፡፡ ይህም የሆነው ከቦርድ ክፋት ይልቅ የእግዚአብሔር ምሕረትና ቸርነት ለወገኖቹ ስለበዛ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት