Thursday, March 31, 2011

የዳላሱ ዓርብ ጉባዔ ከጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ጋር ሊዋሃድ ነው
በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት የወጡት ሁለቱ ካህናት መልአከ ሣህል አወቀና ተሰማና ቀሲስ መስፍን ደምሴ ሕዝቡን በአዳራሽ በማሰባሰብና ወንጌልን በማስተማር ማቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መልአከ ሣህል አወቀ በመኖሪያ ወረቀታቸው ችግር ምክንያት ለዘለቄታው ወደ አትላንታ ቢሄዱም ቀሲስ መስፍን ግን ከጉባኤው አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ጉባኤው በተጠናከረ መልክ እንዲቀጥል ማድረጋቸውም ይታወቃል፡፡

በመሆኑም ቀሲስ መስፍን ባለፈው ዓርብ መጋቢት 16 ቀን ጉባኤው ከተቋቋመ ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ የጉባኤው ደካማና ጠንካራ ጎኖች ምንድን ናቸው ? ወደፊት የጉባኤው መጨረሻስ ምን መሆን ይኖርበታል ? በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ከጉባኤው ወስጥ በተመረጡ ስድስት ሰዎች አማካኝነት አባላቱ ውይይት እንዲያደርጉ በማድረግ ጉባኤው መድረሻው የት እንደሆነ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡

መንበሩ ኢትዮጵያ በሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ በማትመራ ገለልተኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ መቆየትና ፖለቲከኞች ነን የሚሉ አምባገነን የቤተክርስቲያን ቦርድ አባላት በየጊዜው በካህናትና ምእመናን ላይ የሚፈጽሙትን ግፍና በደል እያዩ በዚያ መኖር የክህነቱን ሥልጣንና ክርስትናውን ማዋርድ ሆኖ ስላገኙት ሥራቸውን በፈቃዳችው ለቀው መውጣታቸውን ካህኑ በመግለጥ በአሁኑ ሰዓት ግን የደብረ ጸሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን መደበኛ አገልጋይ ካህን በመሆን እንዲያገለግሉ የተቀጠሩ መሆናቸውንም ለጉባዔው ይፋ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም የስብከተ ወንጌሉን የሠርክ ጉባዔ አገልግሎት ጨምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠብቅባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ በእዚያው በአዲሱ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ውስጥ ለመስጠት እንዳቀዱም ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ አገልጋዮችን የሚያሳትፉ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍሎች እንደተዋቀሩላትና ብዙ ምዕመናንም ቁጭ ብለው ከመማር ተግባር በተጨማሪ ወደ ሚፈልጉት የአገልግሎት ክፍሎች ገብተው የማገልገል ሰፊ እድል እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡በተጨማሪም በአዲሱ መዋቅር ያሉቱን አንዳንድ የአገልግሎት ክፍሎችን ምሳሌ አድርገው በፕሮጄክተር አስክሪን በማቅረብ ሕዝቡ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የኔነት ተሰምቶት ሳይሳቀቅ ማገልገል እንደሚችል በእርሳቸው በኩሉ የተመቻቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ 
እስካሁን በኪራይ እንገለገልበት የነበረው አዳራሽ ባለቤቶች የሌላ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም እኛ የተከራየነው ቦታቸውን እንጂ እምነታቸውን ስላልሆነ በቆይታችን ወቅት የቤተ ክርስቲያናችንን ጠቃሚ ትምሕርቶች ተምረንበታል፡፡ የትምህርት መስጫ አዳራሹ ተሥፋ ቆርጦ የተበታተነውም ሕዝብ ተሰባስቦ እንዲጸልይና ታዋቂ መምህራንና ዘማርያንንም በመጋበዝ በዓይነታቸውና በይዘታቸው እጅግ ልዩ የሆኑ ሦስት ታላላቅ ጉባዔያትም ተደርገውበታል፡፡ ስለዚህ ጉባዔው እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ በመቆት እግዚአብሔርን ሲያገለግል እንደቆየ ሁሉ ወደፊትም የሀሳብና የዓላማ መለያየት ሳይኖር ሰላም በምናገኝበት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ማገልገል እንደሚሻል በመምከር ለእለቱ የተመደበው ጊዜ ስላለቀ ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል፡፡ ወይይቱና ለአዲሱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ኅሊናን የማዘጋጃ መማማሪያዎች በቀሪዎቹ የዓርብ ጉባዔያትም እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡

Monday, March 14, 2011

ደስ ቢለኝም እጅግ አዝኛለሁ
ከወላጆቹ ጋር ቤተክርስቲያን መሄድ የሚያዘወትር አንድ የሰባት አመት ሕጻን ልጅ ካህኑ ‹ እሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኃል፡፡ ከእግዚአብሔር የሚለምን ሁሉ ይሠጠዋል፡፡ › እያሉ ሲያስተምሩ ይሰማል፡፡ ይህን በልጅ አዕምሮው እያሰላሰለ ይሰነብታል፡፡ ከእለታት አንድ ቀን መቶ ዶላር እንዲኖረው በመመኘት እግዚአብሔር ቢሰጠኝ ብሎ አሰበና እንዲህ ብሎ ደብዳቤ ጻፈ፡፡ይድረስ በሰማይ ለምትኖር አምላኬ እግዚአብሔር ፤ስሜ እገሌ ይባላል፡፡ዕድሜዬም ሰባት ዓመት ነው፡፡ ለአንድ ጉዳይ አንድ መቶ ዶላር አስፈልጎኛልና በአስቸኳይ እንድትልክልኝ በአክብሮት እጠይቅሀለሁ ፡፡ በማለት በሚላክለት ሰው አድራሻ ቦታ የእግዚአብሔርን ስም በላኪው አድራሻ ቦታ ደግሞ የራሱን ስም በመጻፍ የወላጆቹን ቤት አድራሻ ያስገባና ደብዳቤውን በፖስታ አሽጎ ያስቀምጠዋል፡፡አንድ ቀን ፖስተኛው ሰው ሲመጣ ይጠብቅና ደብዳቤውን ወደ እግዚአብሔር እንዲልክለት በአደራ ይሰጠዋል፡፡


Monday, March 7, 2011

አዲስ የቤተክርስቲያን ሕንጻ በዳላስ ቴክሳስ !

ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ያልሞላው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የዳላስ ደብረ ጸሐይ ቅዱስ ተክለ ሃማኖትና አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ለቤተመቅደስ አገልግሎት ሊውል የሚችል ትልቅ ሕንጻ በ 900.000 ዶላር መግዛቱ ተገለጠ ፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የዳላስ ከተማ ምዕመናን በተገኙበት ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሕንጻው ለቤተ መቅደስነት ብቁ የሚያደርጉትን መስፈርቶች ለማሟሟላት እንዲችል የ ሪሞዴሊንግ ሥራ እየተሠራለት እንደሆነ ተገልጧል፡፡ ይህ በቅርቡ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ አገልግሎቱን የሚጀምረው ቤተ ክርስቲያን በምድር በርካታ የቢሮና የሕጻናት ማስተማሪያ ክፍሎች፤ የመመገቢያ አዳራሽና መጸዳጃ ቤቶች ያሉት ሲሆን በፎቅ ላይ ደግሞ ሰፊ ቤተ መቅደስና የሰብከተ ወንጌል አዳራሽ ይኖሩታል፡፡