Thursday, July 29, 2010

በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን !

“ነአምን በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት)
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ሐዋርያዊት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። በአንድነቷ ጸንታ፣ በሐርያዊነቷ የአበው ሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት እንዲሁም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ጠብቃ፣ በቅድስናዋ ዕድፍ ጉድፍ ሳይወድቅባት፣ ኃጥአንን ከኃጢአት ርኵሰት የምትቀድስ ናት። የምናምነው፣ የምናገለግለው፣ የምንኖረው ለዚህች እና በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። “በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ስንል ሁሉን በሁሉ ይዘን እንጂ በግማሽ አይደለም። ለሚጠይቁንም ስንመልስ ጊዜውን አይተን፣ የሰዎችን ፊት አይተን ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ተመልክተን ነው።

Wednesday, July 28, 2010

ዘዳላሰ ነኝ ፡፡ከፌስ ቡክ ያገኘሁትን እነሆ ልኬአለሁ ያሉንን የዝግጅታችንን ተካታታይ ከልብ እናመሰግናለን፡፡
የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል !
ይህ የሃገራችን አባባል ብዙ ጊዜ ለሚቸኩሉና በችኮላቸው ጥፋት ለሚያደርሱ ሰዎች መረጋጋት እንዲኖረቸው ለመምከር የሚተረት ወግ ነው፡፡ ቅቤ በክብርና በፍቅር ከሚበሉ ምግቦች መካካል አንዱ ሲሆን አወጣጡና አዘገጃጀቱም በየሃገሩና በየባህሉ የተለያየ ነው፡፡እንደምናውቀው በእኛ ባህል ቅቤን ለማውጣት ወተቱ ጊዜ ወስዶ መርጋት አለበት፡፡ ለዚህ ነው አበው ሰውም ከተረጋጋና ጊዜ ወስዶ ነገሮችን እያስተዋለ ከሠራ ለጥሩ ውጤት እንደሚበቃ ለማመልከት ‹የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል› በማለት የሚተርቱት ፡፡ ከዚህ አንጻር እኛም ስለመረጋጋት ግንዛቤ ታገኙ ዘንድ የሚከተለውን ጽሑፍ በአጭሩ አቅርበነዋል፡፡

Wednesday, July 21, 2010




አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ ! በቤተ ክርስቲያን ከሚቀልዱ ፤ ግፍ ከሚሠሩና ፖሊተከኞች ነን ከሚሉ ኢ-አማንያን እጅና አመራር ቤተ ክርስቲያንህን ታወጣት ዘንድ ስለቤተክርስቲያን ስትል ባፈሰስከው ደምህና በቆረስከው ሥጋህ እንለምንሃለን ፡፡

መለያየት በመካካላቸው ገብቶ የተለያዩትን አገልጋዮችህ የሆኑ አባቶቻችንንም በሃሳባቸው ሁሉ አንድ እንድታደርግለን እንማጸንሃለን፡፡ አሜን፡፡

Monday, July 19, 2010

ትዕቢት እና ትሕትና 
ትዕቢት የትሕትና ተቃራኒ ነው፡፡ትዕቢትን ከሚገልጡት ድርጊቶች መካከል አንዱ የኩራትና የእብሪት ንግግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ንግግራችን ተጠያቂ የሚያደርገን ክፉ ቃላትን ከሚወልደው የትዕቢት ልብ የተነሣ ነው፡፡

ትሑት መሆን የሚሻ ሰው ሰውን ከሚያሳዝንና የሰውን ኅሊና ከሚጎዳ የትዕቢት ንግግር መራቅ አለበት፡፡ ስሜት የሚጎዱ ንግግሮች የምንናገረው ሰዎች ስላስቆጡን ሊሆን ይችላል ፡፡ይሁን እንጂ ቁጣና ኃይል የተቀላቀለበት ንግግራችን ከመንፈሳዊ ሥነ ምግባራችን መገለጫዎች አንዱ የሆነውን ትሕትናችንን በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ስለዚህ ምንጊዜም ቢሆን ቶሎ ከመቆጣትና የሌሎችን ሰዎች ስሜቶች ከሚጎዱ ንግግሮች መራቅ ተገቢ ነው፡፡የትዕቢት ንግግር ሰይጣን የወደቀበትና ክብሩን ያጣበት ክፉ ተግባር ነውና፡፡

ሰው ትዕቢትን ከልቡ ማራቅ ከቻለ የትሕትና ባለቤት ለመሆን አይቸገርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል› በማለት ትዕቢት የውርደት ምልክት ፤ ትሕትና ደግሞ ለሰው ልጆች ክብርና ሞገስን የሚያጎናጽፍ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ምግባር እንደሆነ ይናገራል ፡፡ ያዕ 4፡6


ትሕትና የመንፈሳዊ ሰዎች መገለጫ ጠባይ ነው፡፡ትሑት ሰው ሁሉን ይወዳል ፤ታዛዥና ትዕግስተኛም ነው፡፡ እስቲ ታዲያ እኛም ትዕቢትን ከልባችን አጥፍተን የትሕትና ሰዎች ለመሆን እንሞክር !

Monday, July 12, 2010

እንዳትለያዩ እለምናችኋለሁ !


‹ወንድሞቻችን ሆይ !ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ እንዳትለያዩ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆናችሁ አንድ ቃል ትናገሩ ዘንድ በአንድ ሃሳብም ትመሩ ዘንድ በጌታችን ፤ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥም እለምናችኋለሁ፡፡›1ኛ ቆሮ 1፡10

በሐዋርያው ትምህርት አንድ ልብ አንድ ሃሳብ መሆን ማለት በመልካም ሥራና በሃይማኖት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆን ማለት ሲሆን ልቡናን ከቂምና ከበቀል ከክፋት ንጹሕ በማድረግ የዋህነትን ፤ትህትናንና ንጽሕናን ገንዘብ አድርጎ መገኘት ማለት ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በ 50 ዓ.ም ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ገብቶ ወንጌልን አስተምሮ የቆሮንቶስን ሰዎች ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ፤ ከኃጢኣት ኑሮ ወደ ቅድስና ሕይወት መለሳቸው፡፡ ጌታም ለሐዋርያነት ሲጠራው ‹በአሕዛብ ፊት ስሜን ትሸከም ዘንድ ምርጥ ሐዋርያ አድርጌ ሾሜሃለሁ፡፡ ›ሐዋ 9፡15 ብሎ እንደ መሠከረለት ብዙ አሕዛብን በወንጌል አስተምሮ ወደ ክርስትናው በረት አስገብቷል፡፡

Thursday, July 8, 2010

 ለፈገግታ
በብዙ የዓለም ሀገሮች በተለይም በሃገራችን በኢትዮጵያ ያላውን የኑሮ ሁኔታ ስናስብ በአዕምሮአችን የሚመጣው የብዙኃኑ ሕዝብ ድኅነትና የጥቂት ሃብታሞች ጣራ የነካ የምቾት ኑሮ ነው፡፡ የድኃውና የሃብታሙ ኑሮ ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ነው፡፡ድሃው በእግዚአብሔር ቸርነት የሚኖር እንጂ የሚላስ የሚቀመስ የሌለው ፍጹም ድኃ ነው፡፡ ሃብታሙ ደግሞ የእግዚአብሔር ቸርነት በዝቶለት ገንዘቡን የት ላድርሰው የሚል ቱጃር ነው፡፡ በዚህ መሃል ያለው ደግሞ የድሃና የሃብታም ክልስ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ ድሃውም ሃብታሙም መካከለኛውም እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋና በወሰነለት የኑሮ ደረጃ ይኖራል፡፡ ግን ደግሞ ማኅበራዊ ኑሮ አለና በአጋጣሚ ፤በሃዘን ወይ በደስታ አንዱ ሌላውን የመጎብኘትና የኑሮ ሁኔታውን ማየት እድል ያገኝ ይሆናል ፡፡ብዙ ጊዜ ደሃው ወደ ሃብታም ቤት ለጉልበት ሥራ ወይም ሃብታሙ ሰው ለሚፈልገው ጉዳይ እየጠራው ሊሄድ ይችላል፡፡አልፎ አልፎ ደግሞ ምናልባትም ለቅሶ ካለ ለቅሶ ለመድረስ ሃብታም ወደ ድሃው ቤት ሊሔድ ይችል ይሆናል እንጂ የሃብታሙ እግር ወደ ድሃው ቤት ለመሄድ ያጠረ ነው፡፡ጊዜውም ፍላጎቱም የለውም ፡፡ታዲያ አንድ ድሃ የጉልበት ሠራተኛ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው ቦሌ ሠፈር የሃብታሞችን ቤት የግቢ አትክልት ለመኮትኮትና ሣር ለማጨድ እያሰለሰ ይሄዳል፡፡ሥራውን የጀመረ ሰሞን ጥቂቶቹ ሃብታሞቹ ወደ ቤት ገባ ብሎ ሻይ እንዲጠጣ ይጋብዙታል፡፡ እርሱም ደስ እያለው ይገባና እየተናደደ ይወጣል፡፡

ግን አንድ ቀን እንደህ ሊል ሰማሁት፡፡ የእንጀራ ነገር ሆኖብኝ ነው እንጂ አሁንስ እንደ ሃብታም ቤት መሄድ የጠላሁት ነገር የለም፡፡ እኔም ምነው ለምን አልኩት እሱም የሆነውን ነገር በጥያቄና መልስ አስመስሎ ነገረኝ እኔም ተደነኩኝ በማለት ለፈገግታ ያቀረበልን እኛም ስሙን የማናውቀው አንድ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ነው፡፡ እኛም ከአስተያየት መቀበያ ሳጥናችን ውስጥ ስላገኘነው የላኩልንን ደንበኛችንን ከልብ እያመሰገንን አንባቢዎቻችን እንዲያነቡት በማለት በብሎጉ ፊት ለፊት ሰሌዳ ላይ ለጥፈነዋልና ያንብቡት፡፡

Wednesday, July 7, 2010

ለምኑ ይሰጣችኋል !
                                       ማቴ 7፡7

እግዚአብሔርን ፈልጎ ያላገኘው ፤ ለምኖም ከእርሱ ያልተቀበለ ሰው የለም ፡፡ ቢሮር እርሱ በእግዚአብሔር ያልታመነ ወይም ለጸሎት የሰነፈ ብቻ ነው፡፡ የተራበ ፤የተጠማ ፤ የታረዘ፤ የተራቆተ፤ በችግር የተጎዳና የመሰከነ ሁሉ ቢለምን እግዚአብሔር ሊሰጠው የታመነ አምላክ ነው፡፡

ምክንያቱም እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ‹ ለምኑ ይሰጣችኋል ፤ ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያውን አንኳኩ ይከፈትላችኋል ፡፡ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና ፡፡የሚፈልገውንም ያገኛል፡፡መዝጊያውንም ለሚያንኳኳ ሁሉ ይከፈትለታል፡፡ › በማለት ተናግሯልና፡፡ ማቴ 7 ፡ 7

ከዚህ አንጻር የልመናው ( የጸሎት ) ዘዴው የገባቸው ብልጦች ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በመለመን ብዙ አግኝተዋል፡፡ ስለተደረገላቸው ሁሉ ብዙ አመስግነዋል፡፡ያመሰግናሉም፡፡ ስለዚህ ስለጸሎትና ምስጋና ሰላም ተዋሕዶ ከበራሪ ኢ-ሜይል ያገኘቻትን አጭር የእንግሊዘኛ ጽሑፍ ለአንባቢያን ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘችው እንደሚከተለው ታቀርበዋለች፡፡


Tuesday, July 6, 2010

እንቁላል በመወርወር የሚፈጸም ዝርፊያ
በጭለማና ጭር ባለ አካባቢ ሲነዱ የተወረወረ የዶሮ እንቁላል በመኪናዎ የፊት መስታወት ላይ አርፎ ከተሠበረ የዝናም መጥረጊያ መሣሪያውን ወይም መስታወቱን ለማጽዳት የሚረጨውን ውሃ እንዳይጠቀሙ ይጠንቀቁ ፡፡ በመስታወት ላይ የፈሰሰ የእንቁላል አስኳል ከውሃ ጋር ሲደባለቅና በዝናም መጥረጊያ ሲጠረግ ወተታማ ወይም ደመናማ ቀለምን ይፈጥርና መስታውቱን 92.5 % ያህል ከእይታ አገልግሎት ውጪ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ፊት ለፊትዎን በመኪናው የፊት መስታወት ማየት ስለሚሳኖት ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ አሊያም አደጋውን ለመሸሽ ሲሉ መኪናውን ወደ ዳር አውጥተው ለማቆም ይገደዳሉ ፡፡ በዚህ ጊዜ በአካባቢው የመሸጉና እንቁላሉን በመኪናዎ መስታወት ላይ የወረወሩት ዘራፊዎች በፍጥነት ወደ እርሶ በመምጣት ችግር ላይ ሊጥልዎት ይችላሉ ፡፡ ስለዚህ ይህ አዲሱ የዘራፊዎች የዘረፋ ስልት ነውና መንገድዎን ለእግዚአብሔር አደራ በመስጠት በማያውቁት መንደር በጨለማ ሲነዱ ጥንቃቄ ያድርጉ፡፡

Monday, July 5, 2010

ማሳሰቢያ
ሰላም ተዋሕዶ ላለፉት በርካታ ወራት በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲን ችግሮችና ከዚሁ ጋር በተያያዙ እንዲሁም እውነትን በተመረኮዙ ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ በስፋት ስትዘግብ መክረሟ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚሁ ጋር የአገልግሎት አድማስዋን ከፍ በማድረግ ከዳላስ ውጭ ለማንኛውም የብሎጉ አንባቢ ትምሕርት ይሰጣሉ ተብለው የሚታመኑባቸውን መንፈሳዊና አስተማሪ ጽሑፎችን በማቅረብ ተጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በአክብሮት ትገልጻለች ፡፡

Thursday, July 1, 2010

Marriage is an institution in which a man loses his Bachelor's Degree and the woman gets her masters.
ስለ ትዳርና ጋብቻ በእኛም ሆነ በሌላው ዓለመ ሰብእ ብዙ ተብሏል፡፡ብዙም ይባላል፡፡ በትዳር ውስጥ ስላለ ደስታና ኃዘን ፤ ቁጣና ትዕግስት ወ.ዘ.ተ… በጋዜጣ ፤ በመጽሔት፤ በሙቪና በሌሎችም መገናኛ ብዙኃን በየቋንቋውና በየባህሉ በመዝናኛና በትምህርት መልክ ብዙ ጊዜ ይተላለፋል ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትዳርስ የእነ እገሌ ነው› እየተባለም ይመሰገናል፡፡ ይወደሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‹ትዳር እንዲህ ከሆነስ ቆሞ መቅረት ይሻላል፡፡› እየተባለ ትዳር ሲነቀፍና ሲቀለድበት ይሰማል፡፡ለማንኛውም ባለትዳሮች ትዳራችሁን ዘወር ብላችሁ እንድታዩት ወደ ትዳር ለመምጣት በመንገድ ያላችሁና የወጠናችሁ ሁሉ ትምህርት ታገኙበት ይሆናል በማለት አሜሪካኖች በቋንቋቸው ስለትዳር የከተቧትን ቁምነገር አዘል ቀልድ ከበራሪ ኢ-ሜይል አግኝተን ከዚህ ቀጥለን አቅርበነዋልና አንብባችሁ ተማሩበት፡፡