Friday, November 20, 2009

ምኞት አይከለከልም !

አስተዳደር ባላዋቂ ሰዎች ሲያዝ ውጤቱ ምን እንደሚሆን ዝርዝር ጉዳይ አይስፈልገውም ፡፡ ውጤቱም በዓይን የታየ ስለሆነ ይህ አባባል ግራ የሚያጋባ አይይደለም፡፡

የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ስመ ጥሩና ትልቅ ነው፡፡ይሁን እንጂ ግርማ ሞገስ ያለውና በሥርዓት የታነጸ አስተዳደር ረሀብተኛ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰው ያዝናል፡፡ የቤተክርስቲያኑ ትልቅነትና የአስተዳደሩ Personality ጨርሶ ሊጣጣም ባለ መቻሉ ቦታው ለቦርድ ሥልጣን ሲሉ የአስተዳደር ችሎታ የሌላቸው ሰዎች ሁሉ የሚታገሉበት የጦርነት ሜዳ ሆኗል ፡፡

የሰላም ተዋሕዶ ምኞትና ፍላጎት በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ፈሪሃ እግዚአብሔር ፤ሚዛናዊና ምሁራዊ አስተሳሰብ ያላቸውን እንዲሁም ማስተዳደር የሚችሉ የአስተዳደር ቦርድ አባላትን በቦታው ማየት ነው፡፡ ምኞት አይከለከልም፡፡ ‹ቅን ተመኝ ቅን ያዝልሃል › የሚለው የአበው አባባል በሰላም ተዋሕዶ ኅሊና መመላለስም መልካም እንጂ መጥፎ አይደለም፡፡

የቤተክርስቲያኑ የሥራ አመራር አጀንዳዎች በታክሲ ተራና በየ መንደሩ የሚጠነሰሱ ሳይሆኑ ደረጃ ባለው ቢሮና አዕምሮ ውስጥ የሚቀረጹ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡አስተዳደር በራሱ ሳይንሳዊ ጥናት የተደረገበት ፤ ሕግና ደንብ የተቀረጸለት ሥርዓት ነው ፡፡ ስለዚህ ይህን መርኅ አድርጎ መንፈሳዊነትን በዚህ ላይ እንደ እርሾ ጨምሮ ውጤት ያለውን ሥራ ለመሥራትና ቤተክርስቲያኒቱን ማዕከላዊ ሆኖ ከቡድናዊ አሠራር ነጻ አድርጎ የሚያስተዳድር ቦርድ በዚህ ቦታ ሊፈጠር ያስፈልጋል ፡፡ ለቤተ ክርስቲያኑ የሚታሰብ ከሆነ መሆን ያለበትም ይህ ነው፡፡ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል በሚል መንፈስ እኛ ካልመራናት ይህች ቤተ ክርስቲያን ትፍረስ አሊያም ስትበጠበጥ ትኑር የሚሉ ሰዎች ካሉ በእውነት እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውን እንጂ ቤተክርስቲያኗን የሚወዱ ስላልሆኑ ለእነርሱ ማዘንና ልቦና እንዲሠጣቸው መለመን ተገቢ ነው፡፡

በአንድ የሻይ ክበብ ጨዋታ ላይ አንድ አስተዋይ ሰው ማኅበራዊ ሕይወት ካላሸነፋቸው ለዚህ ቦታ የአስተዳደር ቦርድ አባልነት እኔ እንዲሆኑ የምመኛቸው ሰዎች ብለው የዘረዘሯቸውን ምሁራን የሰላም ተዋሕዶን ቀልብ ስለሳበ ዝርዝራቸውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ቅን ተመኝ ቅን ያዝልሃል፡፡
1. አቶ ሠይፈ ይገዙ - ሰብሳቢ
2. ዶክተር ታዬ - ምክትል ሰብሳቢ
3. አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ - ዋና ጸሐፊ
4. አቶ ግርማቸው አድማሴ - ሕዝብ ግንኙነት
5. አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር - ተቆጣጣሪ
6. አቶ ገረመው ገብሬ - ሒሳብ ሹም
7. ወ/ሮ አያል - ገንዘብ ያዥ
8. …… ዕቃ እቃ ግምጃ ቤት
9. ካህን - የመንፈሳዊ ክፍል ተወካይ ናቸው፡፡

ይህ ሊደረግ የታሰበ ሳይሆን ምኞት ነው፡፡ ዛሬም ቤተ ክርስቲኒቱን የምንወድና ሰላምን የምንናፍቅ ሁሉ ስለ ሥልጣን ፍቅር ማሰብንና መባላትን ትተን ስለ አስተዳደሩ መስተካከል እንጨነቅ፡፡

ከላይ ስማቸው በምኞት ሊስት ውስጥ የተዘረዘሩት ግለሰቦች የታሰቡበት መሥፈርት ፤ የኃላፊነት ድርሻቸውንና ድንበራቸውን አውቀው ይሠራሉ ፤ በካህናት አባቶች የሥራ ድርሻ ውስጥ ጣልቃ ገብነትና ግጭት እንዳይኖር በማስተዋል ተጠንቅቀው ያስተዳድራሉ በሚል ግምት ነው፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ ለቤተክርስቲያኒቱ ልማትና እድገት ፈር ቀዳጅ የሆነ እቅድ ያቅዳሉ በሚል ነው፡፡

ሰላም ተዋሕዶ በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ምእመናን አስተያየታቸውን እንዲሠጡበትና እንዲወያዩበት የአስተያየት መሥጫ መስኮት ያላት ሲሆን በዚሁ በመጠቀም ሃሳብን ማንሸራሸርና ማሳድግ እንደሚቻል ከወዲሁ ትገልጻለች፡፡


No comments:

Post a Comment

አስተያየት