Thursday, July 29, 2010

በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን !

“ነአምን በአሐቲ ቤተ ክርስቲያን፣ በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” (ጸሎተ ሃይማኖት)
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንዲት፣ ሐዋርያዊት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት። በአንድነቷ ጸንታ፣ በሐርያዊነቷ የአበው ሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት እንዲሁም ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ጠብቃ፣ በቅድስናዋ ዕድፍ ጉድፍ ሳይወድቅባት፣ ኃጥአንን ከኃጢአት ርኵሰት የምትቀድስ ናት። የምናምነው፣ የምናገለግለው፣ የምንኖረው ለዚህች እና በዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። “በአንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ስንል ሁሉን በሁሉ ይዘን እንጂ በግማሽ አይደለም። ለሚጠይቁንም ስንመልስ ጊዜውን አይተን፣ የሰዎችን ፊት አይተን ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ተመልክተን ነው።


ማኅበረ ቅዱሳን በተለይም በሰሜን አሜሪካ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያን አንድነቷ ተጠብቆ ይቆይ ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። አሁንም በማድረግ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አቋሙ እና ትምህርቱ በሁሉም ዘንድ ምስጋናን አትርፎለታል ለማለት አያስደፍርም። ገሚሱ ከፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር ሲያገናኘው ሌላው ደግሞ ከአካባቢው ጥቅምና ከሌሎች ፍላጎቶች ጋር ያገናኘዋል። ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማርም ለመማርም የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት፣ ትውፊትና ታሪክ ብቻ መመልከት ከማይበቃበት ደረጃ የተደረሰ ይመስላል። ችግሩ በተለይም በሰሜን አሜሪካ የበለጠ የጠነከረ ሆኗል። ይሁን እንጂ በችግሮቹም መካከል ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እና ጥቅም ከመናገርና ከማስተማር ወደኋላ ልንል አንችልም።

በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ጐራና በዚያ ጐራ ሆነን የተለያየን ሁሉ ግላዊ አመለካከታችንን ትተን ወደፊት ለእኛም ለልጆቻችንም የሚበጀው የቱ ነው? ከሌሎች ትምህርቶቻችንና የአስተሳሰባችን ምንጮች ይልቅ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና እና ሥርዓት ምን ይላል? በዚያ መሠረት እንዳይፈጸም እንቅፋት የሆነው ነገር ምንድን ነው? እኛ ልንፈጽመው አንችልምን? የሚሉትን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም አልፎ ሳናስበውና ሳንረዳው የፓለቲካዊ አስተሳሰብ ልዩነታችን በዚህኛው ላይ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ያንን በሌላ መድረክ መፍታት ይገባልና፡፡

በየአካባቢው ከሥርዓት ውጪ ለሚደረጉ ተግባራት አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ ተባባሪ የሚሆኑ ምእመናን እንደመኖራቸው መጠን አሁን ያለውን ችግር ለመፍታትም የምእመናንን ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ በአስተዳዳር ምክንያት ያልተደሰቱ ምእመናን ራሳቸውን ችለው፣ ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የሚገነጠሉ፤ በሚፈጠሩ ችግሮች የሚያኰርፉት፣ በዚያው በራሳቸው ዓለም ብቻ የሚጓዙ ከሆነ ችግሩን ያሰፉታል እንጂ አያጠቡትም፡፡ በሚያልፍ ችግር የማያልፍ ጠባሳ ጥሎ ማለፍ አይገባም፡፡ በመሠረቱ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት አንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ክፍሉ ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ማቋቋም አይቻልም፡፡ ይህን በመፈጸም ቤተ ክርስቲያንን የበደልን ምእመናን ካለን ምላሻችንን ማስተካከልና መጀመሪያ ራሳችንን ማረም አለብን፡፡ ይህ የመጀመሪያውና ዋናው ለአንድነት የሚደረግ መሠረታዊ መፍትሔ ነው፡፡

ሌላው ምእመናንን የሚመለከተው ጉዳይ ደግሞ ከደጋፊነት መንፈስ ነጻ የመውጣቱ ጉዳይ ነው፡፡ ሰው እንደመሆናችን በተረዳነው መጠን «እነ እገሌ አጥፍተዋል፣ የእነ እገሌ ይበልጣል፣ እንዲያ መሆን ነበረበት፣ እንዲህ መሆን አልነበረበትም» እያልን የምንናገራቸው ሐሳቦች ይኖሩናል፡፡ በእነዚህም ላይ ተመሥርተን ወይም እንደ ዮሐንስ እናት «የእኔ» የምንላቸውንና «አሳቢዎቻቸው» የሆንንላቸውን ልንደግፍ ሌላውንም ልንቃወም እንችላለን፡፡ እንዲህ ያለው ነገር መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን «መለየትን የሚወድ ምኞቱን ይከተላል» ሲል እንደተናገረው መለየትን የመውደድ ምኞትንም የመከተል ድካም ነው (ምሳ.16÷1)፡፡ ስለዚህ “ለቤተ ክርስቲያኔ አስባለሁ” የሚልና የነገውን አርቆ የሚመለከት ሁሉ ከዚህ መንፈስ መላቀቅ፣ ከደጋፊነትም አባዜ መውጣት አለበት፡፡ እንዲያውም «ተበድሏል» ብሎ የሚያስብለትን አካል በራስ አሳብ እያሟሟቁ ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ «ይቅር በሉ» በማለት ኃይልና ድጋፍ መሆን ያስፈልጋል፡፡

ካህናትም ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት አንድ ሆነው መነሣት አለባቸው፡፡ ካህናት አንዲት አጥቢያ መሆን የሚገባትን፣ ቤተ ክርስቲያንም በአጠቃላይ ልትሔድበት የሚገባውንም መንገድ ለምእመናን የማሳየትና የመምራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ካለበለዚያ ቅዱስ ጳውሎስ «አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል÷ በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ÷ ፈቃዱንም ብታውቅም፣ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፤ በሕግም የዕውቀትና የእውነት መልክ ስላለህ የዕውሮች መሪ÷ በጨለማም ላሉ ብርሃን÷ የሰነፎችም አስተማሪ÷ የሕፃናትም መምህር እንደሆንህ በራስህ ብትታመን፤ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን?... በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን? በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና» ሲል በተናገረው አንቀጽ እንያዛለን (ሮሜ2÷17-24)። እኛ ካህናቱ በሥርዓት ሳንመራና ሳንጓዝ ምእመናንን ልንመራና ወደ መንግሥተ ሰማያትም ልናደርሳቸው አንችልም፡፡ እኛ ራሳችንን አንድ ሳናደርግ ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እንዲኖራቸው፤ በወይኑ ግንድ ላይም የተተከሉ ቅርንጫፎች ልናደርጋቸው አንችልም፡፡ ምናልባት “(ምእመናኑ) አይሰሙን ይሆናል፤ በዚህ አሳብ አይሔዱልንም” የሚል ሥጋት ካለ ደግሞ ኃላፊነታችንን የምንወጣበትን፣ እውነትንና ጽድቅን የምንፈጽምበትን መንገድ በጥበብ ማድረግ እንጂ ሳያውቁ በሚያጠፋት ላይ እያወቅን ማጥፋት ከጨመርንበት ጥፋትን እንጨምራለን እንጂ መፍትሔ አናመጣም፡፡ ስለዚህ ካህናት በቁርጥ ኅሊና ለቤተ ክርስቲያን አንድነት መነሣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

አበውም ቢሆኑ ይህንኑ ጉዳይ በደንብ ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ችግሩ በዚህ ባለበት ሁኔታ አይቀጥልም፡፡ ትውልድ ከተረከበው ደግሞ ጭራሹኑ አርአያውና መልኩ ተለውጦ «ከአባቶቻችን የወረስነው ነው» ብሎ፣ በጎ ነገርም መስሎት እንደሙት ባሕር የጥፋት ምልክትና ያለፈበትን ሁሉ እየጐተተ የሚያስቀር እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በአንድ ወቅት በተፈጠረ ክስተት ትልቅ የጥፋት ሐውልት አቁመን እንዳናልፍ የምናስብበት ከአሁን የተሻለ ጊዜም የለም፡፡ ሌላው ቢቀር «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክር ስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» ሲል ቅዱሱ ሐዋርያ ያሳሰበው ነገር ሊዘነጋ አይገባውም (ሐዋ.2ዐ÷28)። ሐዋርያው «... በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ÷ ደቀመዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ» ሲል ለኤፌሶን ቀሳውስት የመከራቸው በእኛ አይደርስም የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ አበውም ለዚህ አንድነት የሚከፍሉትን ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈልና አርአያ ሆኖ ለማለፍ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ያላቸው አይመስልም፡፡ አባቶች ሆይ ቅዱስ ጳውሎስ «ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ» ብሎ የተናነገረለትን ፍቅር እናንተስ ለምን አታሳዩንም? ክፉውን በበጎ ማሸነፍስ ከማን እናያት ይሆን?

ወጣቶችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎችም ሁላችንም ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ልንተጋና ጉዳይ አድርገን ልንወያይበት፤ ቢያንስ በአሳብ ደረጃ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደ አንድነት ለማምጣት ቆርጠን መነሣት ይገባናል፡፡ ጌታ በወንጌል «ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል፡፡ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበስቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና» ሲል የገባልንን ቃል ኪዳን እንዲፈጽምልን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ አሳብ መሆን ያስፈልገናል (ማቴ.18÷19)። የአሳብ አንድነቱ የሚሆነውም ቢያንስ «ቤተ ክርስቲያናችን አንድነቷን መያዝ አለባት፤ ሁሉም አካል ለዚህ አንድነት መሥራት አለበት፤ ለአንድነቱ አስተዋጽዖ የሚያደርግ እስከሆነ ድረስ ማንኛውም ጥቅማችንን ይቅርብን» የሚሉት ላይ መሆን አለበት፡፡ ያን ጊዜ «በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል» የተባለው ይፈጸምልናል፡፡ ስለዚህ ከአበው ጀምሮ ከካህናት፣ ከመምህራን፣ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶችና ከመላው ምእመናን የሚጠብቀው የሚፈለገውም ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት መጋደል ነው፡፡ «እነሆ የተወደደ ሰዓት አሁን ነው፤ እነሆ÷ የመዳን ቀን አሁን ነው፡፡ አገልግሎታችንም እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም» ተብሎ እንደተጻፈው ጊዜው አሁን ነውና ሁላችንም ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ድርሻችንን እንወጣ (2ኛ ቆሮ.6÷2)።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ አሜን

በኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ን የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን
የአሜሪካ ማዕከል

No comments:

Post a Comment

አስተያየት