Monday, July 19, 2010

ትዕቢት እና ትሕትና 
ትዕቢት የትሕትና ተቃራኒ ነው፡፡ትዕቢትን ከሚገልጡት ድርጊቶች መካከል አንዱ የኩራትና የእብሪት ንግግር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ንግግራችን ተጠያቂ የሚያደርገን ክፉ ቃላትን ከሚወልደው የትዕቢት ልብ የተነሣ ነው፡፡

ትሑት መሆን የሚሻ ሰው ሰውን ከሚያሳዝንና የሰውን ኅሊና ከሚጎዳ የትዕቢት ንግግር መራቅ አለበት፡፡ ስሜት የሚጎዱ ንግግሮች የምንናገረው ሰዎች ስላስቆጡን ሊሆን ይችላል ፡፡ይሁን እንጂ ቁጣና ኃይል የተቀላቀለበት ንግግራችን ከመንፈሳዊ ሥነ ምግባራችን መገለጫዎች አንዱ የሆነውን ትሕትናችንን በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ስለዚህ ምንጊዜም ቢሆን ቶሎ ከመቆጣትና የሌሎችን ሰዎች ስሜቶች ከሚጎዱ ንግግሮች መራቅ ተገቢ ነው፡፡የትዕቢት ንግግር ሰይጣን የወደቀበትና ክብሩን ያጣበት ክፉ ተግባር ነውና፡፡

ሰው ትዕቢትን ከልቡ ማራቅ ከቻለ የትሕትና ባለቤት ለመሆን አይቸገርም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል› በማለት ትዕቢት የውርደት ምልክት ፤ ትሕትና ደግሞ ለሰው ልጆች ክብርና ሞገስን የሚያጎናጽፍ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ምግባር እንደሆነ ይናገራል ፡፡ ያዕ 4፡6


ትሕትና የመንፈሳዊ ሰዎች መገለጫ ጠባይ ነው፡፡ትሑት ሰው ሁሉን ይወዳል ፤ታዛዥና ትዕግስተኛም ነው፡፡ እስቲ ታዲያ እኛም ትዕቢትን ከልባችን አጥፍተን የትሕትና ሰዎች ለመሆን እንሞክር !

No comments:

Post a Comment

አስተያየት