Friday, September 10, 2010

በአዲስ ዓመት አዲስ ፍሬ

ስማቸውንና ምንጩን ሳይጠቅሱ ይህን ትምህርታዊ ጽሑፍ በአድራሻችን የላኩልንና የዝግጅታችንን ተከታታይ ከልብ እያመሰገን ትምህርቱ ወቅታዊ ሆኖ ስላገኘነው እኛም አንባቢያን እንዲማሩበት በማለት አቅርበነዋል።

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ በእለተ ረቡዕ ቀንና ሌሊትን ብርሃንና ጨለማን የሚለዩ ለዕለታትታት ለወራትና ለዓመታት መቁጠሪያ የሚያገለግሉ በሰማይ ጠፍር ላይ ብርሃናት ይሁኑ ብሎ በማዘዝ ጸሐይን በቀን ጨረቃንና ከዋክብትን በሌሊት እንዲያበሩ ፈጥሯል። እነዚህም ፍጥረታት ከተፈጠሩበት ዕለት ጀምሮ የተፈጠሩበትን አላማ ሳያዛቡ የፈጣሪን ትእዛዝ ሳያጓድሉ ክረምትንና በጋን ሲያፈራርቁ ሰዓታትን በዕለታት እለታትን በሳምንታት ሳምንታትን በወረት ወራትንም በአመታት እያፈራረቁ ለሰው ልጅ ሕይወት ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ። ኦሪት ዘፍ1፥14፡19

በዘመናት ሂደት ውስጥ ትውልድ ይሄዳል ትውልድ ይመጥል። በዚህ የጊዜ ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ ይጸነሳል ይወለዳል ያድጋል ኋላም ይሞታል። በእንደዚህ አይነት የሕይወት ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ የጋራ የሆነ ተመሳሳይ ባህርይ ቢኖረውም ከውልደቱ ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞቱ ባለው የምድር ላይ የሕይወት ቆይታው እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ የሕይወት ታሪክ አለው። በዚህ ምድራዊና ጊዚያዊ በሆነ ሕይወቱ ደስታና ሀዘን ማግኘትና ማጣት መውደቅና መነሳት ይፈራረቁበታል። የሰው ልጅ ግን በእግዚአብሔር አርያና ምሳሌ ሲፈጠር የእግዚአብሔርን ሕልውና አውቆ ሕጉንና ትእዛዙን ጠብቆ አምላኩን አመስግኖ ክብሩን ወርሶ እንዲኖር ነበረ። በዚህም ተፈጥሮው ለዘላለም እንዲኖር እንጂ ለጊዜያዊ ሕይወት ታይቶ እንዲጠፋ ለሞት የተፈጠረ አልነበረም።

ሕጉን ትእዛዙን ሲጥስ ግን ክብሩን አጥቷል ጸጋው ተገፏል። ዘላለማዊ ሕይወትን ያጣ ሟችና ጊዜያዊ ለመሆን ችሏል። በዚህም ውድቀቱ የተነሳ ሰው ልጅ ረጅም የዘመናት ጉዞውን የችግር የመከራና የጭንቅ እንዲሆን አድርጓታል። ዘመኑንም የፍዳና የመርገም ዘመን አሰኝቶታል። አምላካችን ግን ቸርና ይቅር ባይ በመሆኑ እንደ ሰው በደል ሳይሆን እንደቸርነቱ የፍዳውን ዘመን በታላቅ መስዋዕትነት ወደ ምህረት ዘመን ለውጦታል። ዛሬ እኛ ያለንው በዚህ የምህረት ዘመን ውስጥ ነው። ይህ ማለት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ምህረት ያገኘበትን የይቅርታ ዘመን ያሳየናል። ይህን የምህረትና የይቅርታ ዘመን እያንዳንዳችን በተገቢው መንገድ ልንጠቀምበት ይገባል።

«ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ...ሌሊቱ አልፏል ቀኑም ቀርቦአል እንግዲህ የጨላማን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ በቀን እንደምንሆን በአግባቡ እንመላለስ በዘፈን በስካር አይሁን በዝሙትና በመዳራት አይሁን በክርክርና በቅንአት አይሁን» ሮሜ 12፥11 ሲል ቅዱስ ጳውሎስ ይመክረናል። የብሉይ ኪዳን መጨረሻ የአዲስ ኪዳን መጀመሪያ በመሆን ከጌታ ዘንድ የተላከው መጥምቁ ዮሐንስ የምህረት ዘመን መቅረቡን እያወጀ ሲመጣ የሰው ልቡና ከኃጢያት ከትዕቢትና ከአመጽ ተላቆ ትህትና እና ፍቅርን ገንዘብ እንዲያደርግ «የእግዚአቤሔር መንግስት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ሰብኳል። ማቴ 3፥5 አንድ ዘመን በራሱ አዲስ ነው የሚባለው የሰው ልጅ በሕይወቱ ከኃጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከጨላማ ወደ ብርሃን፣ ከክፋት ወደ ደግነት፣ በንስሐ ሲመለስ ነው። ዘመን ያለፍንበትን ጊዜ ወደ ኃላ ዞር ብለን የምናይበት ምስታወት ነው። በዘመን መስታወትነት ራሳችንን ስናይ ከተፈጥሮችን ጋር አብረውን የማይሄዱትን የኃጢያት ቆሻሻዎች ከላያችን ላይ ልናራግፍ ይገባል። አለበለዚያ ባሳለፍነው ዘመናት ውስጥ ከክርስትና ሕይወታችን ጋር የማይስማሙትን ተግባራት ሳናስወግድ ራሳችንን ሳናስተካክል ከዘመን ዘመን መሸጋገሩ በዕድሜ ላይ እድሜ መጨመሩ ብቻ ጥቅም የለውም። እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍስሐ ነውና እርሱ የሚሰጠን። በዚህ ምድር ላይ በሕይወት የምንቆየው ለተወሰነ ጊዜ ነው።

 በዚህ ቆይታችን የምንኖርበት ዘመን የሰላም እንዲሆን ከፈለግን ከክፉ ነገር ልንርቅ ይገባል። «ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል። ከክፉ ፈቀቅ ይበል» 1ጴጥ3፥10 ይላል። ኋላም የማያልፈውንና የማይጠፋውን ዓለም ለመውረስ እንድንችል በመንፋሳዊ ሕይወታችን ፍሬ ልናፈራ ይገባል። ፍሬ አፍርተን ለመገኘት የሕይወት ግንድ ከሆነው ከመድኃኔ ዓለም ጋር ኅብረት ሊኖረን የገባል። ከእርሱ ከተለዩ ፍሬ ማፍራት አይቻልምና። «አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል። እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል» እንዲል ። ማቴ 3፥9 ፍ በዚህ አዲስ ዘመን በንስሐ ሕይወት ተመላልሰን መልካም ፍሬን፡ ለመገኘት እንዲያበቃን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን የበረከት የሰላም የፍቅር ዘመን ያድርግልን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም አማላጅነት አይለየን። አሜን

1 comment:

  1. ሰላም ተዋህዶዎች እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሳችሁ

    የዚህን ትምህርት ምንጭ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። ጽሑፉ የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤ/ክ እያዘጋጀ ከሚያሰራጨው "መልእክተ ሰንበት" ተብላ ከምትታወቀው ሳምንታዊ መጽሔት የተወሰደ ነው።

    ከዚህ ቀደምም እንዲሁ Aug 07 2010 "ነፋስም ወደ ፊታቸው ነበር" በሚል ርዕስ ከመልእክተ ሰንበት ሳምንታዊ መጽሔት የተወሰደ ወጣ ትምህርት በብሎጋችሁ ላይ ወጥቶ አንብቤያለሁ።

    ምናልባትም ሳምንታዊ መጽሔቷ እንድትደርሳችሁ የምትፈልጉ ከሆነ በኢሜይላቸው ብትጽፉላቸው ኢሜይላቸው atl.abo.eotc@gmail.com መሆኑን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።

    መልካም አዲስ አመት

    ReplyDelete

አስተያየት