Sunday, May 16, 2010

የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባዬ ሆይ ነው !

ከላይ ለዚህ ጽሑፍ ርእስ የሆነውን ዓረፍተ ነገር ‹የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ› ነው፡፡ የሚለው የአገራችን ይትበሀልና ተረት የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ ሰንበቴ የሚባለው የቦርድ ልሳን የሆነው ብሎግ ከጀመረበት ቀን አንስቶ እንደ ሞኝ ዘፈን ወይም ለቅሶ መላልሶ የሚያሰማው አንድ ነገር አለው፡፡ ይህ ደግሞ ቦርድን በምን መንፈስ እንደሚያስብና እንደሚሠራ ለማን ሲል ደግሞ መከራውን እንደሚያይ በግልጽ መረዳት የሚያስችልና የሚጠቁም ነው፡፡

የአስተዳደር ቦርዱ የክርስትናውን መንገድ ይዘው የሚጓዙ አማንያን ክርስቲያኖችን በሃይማኖት ሆኖ ማገልገል አይፈልግም፡፡ ለዚህ ችሎታውም ብቃቱም የለውም፡፡ከዚህ ይልቅ ቦርዱ በብሎጉ ልሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በተደጋጋሚ እየለፈፈ ያለው ለመንፈሳዊ ጉዳዮችና ለአስተዳደራዊው ችግሮች አንጻራዊ መፍትሔዎችን ሳይሆን በከሠረ የፖሊቲካ ፕሮፓጋንዳ ፖርቲ መሰል መግለጫዎችንና ቅስቀሳዎችን ነው ፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ከውስጣቸው ያሉ ጥቂት የቦርድ አባላት በተዘበራረቀ፤ በተምታታ፤ መያዣና መጨበጫ በሌለው የፖለቲካ መንፈስና ከውጭ ባሉ መሰል ሰዎች በሚደረግባቸው ግፊት ለመሥራት ስለሚሞክሩ የሥራዎቻቸው ውጤቶች ሁሉ ከክርስትናው መንገድ መረን ለቀው የወጡና አደጋን በቤተክርስቲያኒቱ ላይ የጋረጡ ናቸው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ፤ የወያኔ መንግሥት ፤ አባ ፓውሎስ ወዘተ…እያሉ ዘወትር የሚጮሁት ጩኸት ‹ የሞኝ ዘፈን …› ሚለውን ተረት እንዲተረትባቸው አድርጓል፡፡ የሚጠቀሙባቸው እነዚህ ቃላት በኢትዮጵያ መንግስት ፖለተካ ላይ ተቃውሞ አለኝ የሚለውን ሕዝብ ለማሰባሰብና በሃይማኖቱ ሽፋን የፖለቲካውን ክስረት በዚህ ለለመሸፈንና በቤተክርሰቲያኒቱ ስም አንዳንድ የጥቅም መንገዶችን ለማስተካከል ነው፡፡ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርሰቲያን ከላይ ከተጠቀሱት ሃይማኖታዊም ሆነ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በሰላምም ይሁን በጠብ ምንም ግንኙነት የሌላት ስትሆን ያለችበትም አስተዳደራዊ አቋም ገለልተኛ ነው፡፡
ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው የፖለቲካው ስሜት እንጂ እውቀቱ የሌላቸው ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ነን ባዮች በቤተክርስቲያኒቱ ያለውን ሰላም በማደፍረስ መድረክ ለማግኘት የሚያደርጉትን ሩጫ ሕዝበ ክርስቲያኑ ጠንቅቆ በመራዳት እንደመዥገር በቤተ ክርስቲያኒቱ ጀርባ ላይ የተጣበቁትን ነቀርሳዎች መንቀል ይጠበቅበታል፡፡
የቦርድ ልሳን የሆነው የሰንበቴ ብሎግ የሚያወጣቸው መልእክቶቹ ሁሉ ፖለቲካዊ መንፈስ ያላቸው ይምሰሉ እንጂ በፖለቲካዊው ሚዛን ሲመዘኑ ደግሞ ብስለትና ጭብጥ የሌላቸው አሉባልታዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካንና ፖለቲከኛን በትክክለኛው ትርጉም ካየነውና ፖለቲከኞች ነን ከሚሉትና በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቦርድ ጉያ ውስጥ ምሽግ ሠርተው ከተደበቁ አስመሳዮች ጋር ስናነጻጽረው ፍየል እዚህ ቅዝምዝም እዚያ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን ከአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ተቋም (ማኅበረ ቅዱሳን) ጋር እያገናኙ አሉባልታን ማናፈስ ፤ ምንም ይሁን ምን አንድን ትልቅና አገር መሪ ፓርቲንና መንግሥትን ወያኔ እያሉ ከአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ጋር የትጥቅ ትግል ገጥመው በጦር ሜዳ እየተዋጉ ያሉ ይመስል በሰንበት ወረቀት ላይ ስም እየተቀሱ መሳደቡ ፤ አንድን ትልቅ የቤተክርስቲያንን መሪ ማንቋሸሽና መዝለፉ ፖለቲከኛ የሚያደርግ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሰዎች ፖለቲከኞች ናቸው የሚል የኩራት ስያሜ ይሰጣቸው ነበር ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካኛ ትርጉምና ሚዛኑ በዚህ የሚገለጽ አይደለምና እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ፖለቲከኞች ተብለው የሚጠሩ ሳይሆን ትክክለኛ ስያሜያቸው ወረኞች ወይም አሉባልተኞች የሚለው ነው፡፡
ስለዚህ የቦርድን ስህተትና ጥፋት ለመሸፈን ማኅበረ ቅዱሳን ፤ ወያኔ ወይም አባ ፓውሎስ ወዘተ… እያሉ በየጊዜው አሉባልታ መንዛት የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ ነውና ይህን የከሠረ ፖለቲካ ትታችሁ ሕዝበ ክርስቲያኑ መረጋጋትና ሰላም በቤተ ክርስቲያኑ እንዲያገኝ እጃችሁን ወደ ሰላም ብትዘረጉ የተሻለ ይሆናል፡፡

2 comments:

  1. የዳላስ ከተማ ፖለቲከኝነት ፖሊስ ጠርቶ ሕዝበ ክርስቲያንን በቤተ መቅደስ ውስጥ ማስደብደብ ከሆነ ፖለቲካ በአፍንጫዬ ይውጣ!

    ReplyDelete
  2. ሰዎቹ ሃይማኖቱም ፖለቲካውም አላማረባቸውም አርፈው ቢቀመጡ መልካም ነበር እንኳን ለሃይማኖተኛነት ለፖለቲከናነትም መስፈርት እንዳለው ማወቅ አለባቸው በጣም ያሳዝናል ኢትዮጵያዊ ሁሉ በነሱ የተነሳ አፈረ ሰላምና ፍቅር ይስጠን ,,,,,,,,,,

    ReplyDelete

አስተያየት