Tuesday, December 8, 2009

አሸናፊው ማና ነው ? ተሸናፊውስ ?

ከላይ በርእሱ የተቀመጠውን ጥያቄ በትክክል የሚመልሰው የፍርድ ቤቱ ውሣኔ ነው ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች በቦርድና በከሳሾች መካከል የተጀመረውን ክስ አስመልክተው በሚሰጡት አስተያየት አሸናፊና ተሸናፊ የለም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ በፍርዱ ፍጻሜ የግድ አንዱ ይሸነፋል ሌላው ደግሞ ያሸንፋል፡፡

ከሻሾች ፤ የአስተዳደር ቦርዱን ሕግን በመጣስ ይሠራል ፤ የነበረውን የቤተክርስቲያኑን መተዳደሪያ ሕግ ያለ አባለቱ ፈቃድ መብት አለኝ ብሎ ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ ቀይሯል ፤ ይህንኑ አዲስ ሕግ በመጠቀም ደግሞ ብዙ አባላትን ከአባልነት ሠርዟል፤ማስተዳደር ባለመቻሉ ቤተክርስቲያኒቱን ለኢኮኖሚያዊ ውድቀት ዳርጓታል ወዘተ… በማለት ከሠዋል፡፡

አስተዳደሩ ደግሞ የምሠራው ሁሉ ትክክል ነው ብሎ እየተሟገተ ነው ፡፡ በዚህ የክስ ሂደት ሁለት ሶስት የሚሆኑ ንዑሳን ሽንፈቶችና አሸናፊነቶችም በየደረጃው ታይተዋል ፡፡ የክሱ ሂደት ተጠቃሎ ሁለቱንም አካላት የሚገላግል የመጨረሻ ፍርድና ውሣኔ ሲሰጥ ደግሞ የግድ አንዱ ይረታል፤ ሌላው ደግሞ ይረታል፡፡ በዚህም አንዱ አሸናፊ ሌላው ደግሞ ተሸናፊ ይሆናሉ፡፡

ለምሳሌ አስተዳደሩ ከሳሾችን በማግለል በራሱ መንገድና ባወጣው አዲስ ደንብ መሠረት ሊያካሂድ የነበረውን ምርጫ ከሳሾቹ ማስቀረታቸው በአስተዳደሩ በኩል የነበርውን ዕቅድ አክሽፏልና ለቦርዱ ንዑስ ሽንፈት ነው፡፡ ለከሳሾቹ ደግሞ ተሥፋ ሰጪ ንዑስ ድል ነው፡፡ ይህ ንዑስ ሽንፈትና አሸናፊነት መሥመሩን ጠብቆ ወይም በተገላቢጦሽ ጉዞ ወደ ዋናው ድልና ሽንፈት ይደርሳል፡፡

አያድረገውና በክሱ መጨረሻ ለቦርዱ ከተፈረደ ቦርዱ ፈላጭ ቆራጭነቱን በሕግ አረጋግጧልና አሸናፊ ይሆናል፡፡ አሸናፊነቱን ተመርኩዞ እስካሁን ተግባር ላይ ለማዋል የተቸገረበትን የበቀል ሥራዎች ሁሉ በግልጽ ተግባራዊ ለማድረግ ይነሣል፡፡ ከሳሾችም ተሸንፈዋልና አዲሱን የባርዮሽ ሥርዓተ ማኅበር ሳይወዱ ለመቀበል ይገደዳሉ፡፡ አሊያም የራሳቸውን ውሣኔ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡የትግሉ ዋና ዓላማ ግን አባላት የእግዚአብሔር እንጂ የአምባ ገነኑ ቦርድ ባርያና ሎሌ እንዳይሆኑ ለማድረግና ለመከላከል ነው፡፡

በሌላም መልኩ ደግሞ ከሳሾች ከተፈረደላቸው የቦርድ አባላትን ከሰውነት ተራ ወደ አማልክት እንዲቀየሩና ጣዖት ሆነው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እዲመለኩ የሚረዳቸውን አዲሱን ባይሎ ገደል የሚሰድና የቤተክርስቲያኒቱን እንዲሁም የአባላትን ሙሉ መብት የሚያረጋግጥ በመሆኑ አሸናፊዎች ይሆናሉ፡፡በአንጻሩም ደግሞ ቦርድ ያሰበውና ያቀደው የተንኮል ሤራ ሁሉ በፍርድ ቤቱ ውሣኔ እስካሁን እንዳየነው ስለሚከሽፍበት ተሸናፊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ስለዚህ በፍርድ ቤቱ ሂደት አሸናፊና ተሸናፊ እነዚህ ሁለት ውጤቶች በግድ የሚጠበቁ ናቸውና ከጉዞአችን አንዘናጋ ! ከፍርድ ቤቱ ውሣኔ በኋላ ሊከሠት ይችላል ብለን ስለምናስበው ትርምስ ከሆነ የምንሰጋው ከሕግ በላይ መሆን የሚችል የለምና እዚያው ያድረሠን ፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት