Tuesday, December 15, 2009

ንጋት ቀትርና ምሽት


ሊነጋ ሲል ይጨልማል!ግን ለጊዜው ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ጎሕ ይቀዳል፡፡ ውጋገኑን ተከትሎ ደግሞ ይነጋል፡፡ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ጸሐይ ትወጣለች ፡፡በዘገምተኛ ጉዞዋ ጸሐይም ቀስ እያለች ምድርንና በላይዋ ያሉትን ሁሉ እያሞቀች ወደ ቀትር ትደርሳለች፡፡

በቀትር ወይም በእኩለ ቀን ላይ ጸሐይ ኃይሏ ይጸናል፤ ትኩሳቷም ይጨምራል ፡፡በዚህ ጊዜ ጸሐይን በምግብነት ይጠቀሙባት የነበሩ ዕጽዋትም ከሙቀቱ ብርታት የተነሣ መዛል ይጀምራሉ፡፡ውሃ ሲያገኙ ደግሞ ይጸናሉ፡፡ ከብቶችም የሣር ግጦሽ ተግባራቸውን አቁመው ሐሩሩን ለማሳለፍ ወደ ዘፍ ጥላ ያዘግማሉ፡፡ በዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጠው ያመሰኳሉ ፡፡ደግ እረኛ ካላቸው ደግሞ የጸሐይ ትኩሳት ትንሽ ቀዝቀዝ ሲል ውሃ ቢጤ ቀምሰው ወደ ግጦሻቸው ይመለሳሉ፡፡ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ በዚያ ሲግጡ ያመሻሉ፡፡

ሰዓቱን ጠብቆ ጨለማ ደግሞ ይመጣል ፤ ምድርም ትጠቁራለች፡፡ለማረፍ የታደሉ ፍጥረታት ሁሉ በእንቅልፍ ያሸልባሉ፡፡ተፈጥሮ የቀን ውሎአቸውን በዱርና በዋሻ የወሰነላቸው አራዊት ደግሞ ተራቸውን ጠብቀው የእለት እንጀራ ፍለጋ ለአደን ይወጣሉ፡፡በዚህ መዘውር ቀንና ሌሊት ይፈራረቃሉ ፡፡ ይመሻል ይነጋል፡፡

ውጋገን ወይም ንጋት የብሩህ ተሥፋ ምሳሌ ነው፡፡ ውጋገን የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እግዚአብሔር ለተገፉ ይፈርዳል፤አባላት ያጣቱን መብትና ነጻነት በእግዚአብሔር ኃይል ያገኛሉ ብለው በተሥፋ የሚጠብቁት ሕይወት ነው፡፡ ,አምላካችን እግዚአብሔር ከዚህ ከሚነደው እሳት ያድነናል ባያድነንም እንኩዋን አንተ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም፡፡ . ዳን 3:17 እንዳሉት ሦስቱ ህጻናት ተገፍተናልና እግዚአብሔር ይፈርድልናል ብለው የተጠቁ ሰዎች የሚጠብቋት የፍርድ ቀን ናት፡፡ ውጋገን እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ዛሬ ባይፍርድልንም እንኩዋ ነገ አርነት ያወጣናል ብለው ክርስቲያኖች ብርሃንን ለማየት የሚናፍቋት የተሥፋ ዕለት ናት ፡፡

ቀትር ደግሞ የፈተናና የብዙ ችግር ጊዜ ምሳሌ ነው፡፡ ቀትር የበጎ ነገር ጠላት የተባለ ሰይጣንም ኃይሉ የሚበረታበት ሰዓት ነው፡፡ሰይጣን ተፋቅረውና ተከባብረው እንዳይኖሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች የተለያዩ ፈተናዎችን ያመጣል ፡፡በዚህም ክርስቲያኖች በጽኑ ይፈተናሉ፡፡ በፈተናውም ብዛት ይዝላሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሕይወት ውሃ ነውና ቃሉን የሚጠጡ ሁሉ ከዝለታቸው ይበረታሉ፡፡በቃሉ ኃይል የሚበረቱ ሁሉ የሚመጣውን ፈተና ሁሉ በትዕግስት ያልፋሉ፡፡

ይህ አሁነው ያለንበትም ወቅት የቀትር ሰአት ነው፡፡ከቤተ ክርስቲያኗ መቆርቆር ጀምሮ ብዙ የደከሙ አባላት አናቃችሁም ተብለው ተገፍተዋል፡፡ አማንያን ተረጋግተው እንዳያመልኩ ታውከዋል ፡፡ የአስተዳደር ቦርዱም ችግርና ፈተና ውስጥ ወድቋል፡፡ ከሊቅ አስከ ደቂቅ በቤተክርስቲያኑዋ የአሁን ጉዞ ደስተኛ አይደለም፡፡ ሁሉም በመንፈሳዊ ሕይወቱ ዝሏል፡፡ሁሉም ነገር ያልፋል፡፡ ግን እስኪያልፍ ያለፋል እንደተባለው ሳንናወጥና ከሃይማኖታችን መሥመር ሳንወጣ የበረታው የፈተና ሐሩር እስኪያልፍ ድረስ በቤተክርስቲያኒቱ የእምነት ጥላ ሥር መቀየት አስፈላጊ ነው፡፡ ‹በፈተና የሚጸና የተባረከ ነው፡፡ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተሥፋ ስለ እርሱ የሠጣቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላል፡፡ › ተብሏልና ፡፡ያዕ 1፡12

ምሽት ወይም ሌሊት እግዚአብሔር አምላክ ለክርስቲያን ወገኖቹ ከብዙ ፈተና በኋላ የሚሰጣት የሰላምና የመረጋጋት ጊዜ ምሳሌ ናት፡፡ ምሽት ፤ በቀን ውሎው ሲደክም የዋለ የሰው ልጅ ሁሉ በየቤቱ ተከቶ በመኝታ እረፍት የሚያደርግባት ጊዜ ናት፡፡ የምናወራው እግዚአብሔር በሠራው የተፈጥሮ ሥርዓት ‹ቀኑን ለሠራዊት ሌቱን ለአራዊት› በሚለው መርህ መሠረት ስለሆነ አሁን የምንኖርበትን አለም ተገላቢጦሽ የሥራና የመኝታ ሥርዓት ጠባይ በጠበቀ መልኩ ላይሆን ይችላል፡፡

ባለመደማመጥና ባለመወያት ፡ በመናናቃችንና ባለመከባበራችን ከአስታራቂ ሽማግሌዎች ድንበር አለፍን፡፡ የአንድ ሃገር ልጆች ፤የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተለይም የአንዲት ቤተክርስቲያንና ሃይማኖት ተከታዮች የሆን ክርስቲያኖች ተካሰን በፍርድ ቤት ቆምን፡፡ ፍትህንም ከዚያ እየጠበቅን ነው፡፡ ግን ይህ የሚቆመው መቼ ነው ? ሲሰለችንና ጉልበታችን ሲያልቅ ? ወይስ ገንዘባችን ሲያልቅ ? ይህን ከእኛ ይልቅ እግዚአብሔር ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሥራና ድካማችን እናርፍ ዘንድ ግን የምሽቱ ጊዜ ፈጥኖ ይመጣልን ዘንድ ያስፈልገናል፡፡

በደልና ኃጢኣታችንን ሳይመለከት ከዚህ ከተበላሸ አካሄዳችን መልሶ ፤ ምሽቱን አቅርቦ የሁላችን ክርስቲያኖች ቤት በሆነች በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን በምሽት ለመሰብሰብ ያብቃን፡፡
እስቲ ይህን ስብከት በማድመጥ እራሳችንን እንመልከት








No comments:

Post a Comment

አስተያየት