Monday, January 31, 2011

ለመልአከ ሣህል አወቀ አሸኛኘት ተደረገላቸው !
በኤፕሪል 25 2010 የዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳደር ቦርድ መልአከ ሣህል አወቀን በውድቅት ሌሊት በፖሊስ አስገድዶ በማስፍረም በክህነት ከሚያገለግሉበት የሥራ ገበታቸው ላይ እዲሰናበቱ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ የግፍ አሠራር በመመልከት ቀሲስ መስፍንም ሕዝቡን በዓውደ ምህረት ተሰናብተው በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን በመልቀቅ መውጣታቸውም ይታቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ የአስተዳደር ቦርዱ የቀጠራቸው ኬጂ 9 ቦምብ ፈታሽ ፖሊሶች ወደ ቤተ መቅደሱ በድፍረት ከነጫማቸው በመግባት ምእመናን ከጸሎት ገበታ ላይ በኃይል በመጎተት ደብድበዋል፤ በካቴና ብረትም ጠፍረው በማሰርም አሰቃይተዋል፡፡ ይህም በቴሌቪዥን የታየ ፤ ዓለምን ያስደነቀና ያስቆጣ አስገራሚ ክስተት ብዙዎችን ከቤተክርስቲያኒቱ አሽሽቷል፤አንዳንዶቹንም ሃይሞኖታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል፤ በርካታ የቤተክርስቲኒቱ ምእመናንም በመተባበር ድርጊቱንና አምባገነናዊውን የቦርድ አስተዳደርን በሕግ በመቃወም ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንዲመለከተው አድርገዋል፡፡ 

በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትና ክብር ያላቸው እነዚህ ሁለቱ መምህራን ካህናት ግን የተቀበሉትን የክህነትና ከፈጣሪ የተሠጣቸውን መንጋውን የመሰብሰብ ኃላፊነት በመገንዘብ የተበተነውን ሕዝብ በማሰባሰብ፤ በቃለ ወንጌል በማረጋጋትና በማጽናናት ለተጎዳው ህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽዎ አበርክተዋል ፡፡ ለዚሁም ዘወትር ዓርብ ከምሽቱ 7.00 ጀምሮ የስብከተ ወንጌል መርኃ ግብር በመዘርጋትና ታላላቅ ትምሕርታዊ ጉባዔያትን በየሦስት ወሩ በማዘጋጀት ምዕመናኑን በቃለ ወንጌልና በዝማሬ አገልግሎት እንዲረኩ በሃይማኖታቸውም እንዲጠነክሩ ማድረጋቸው የበጎ ሥራቸው ዋቢ ምስክር ነው፡፡ 
ይሁን እንጂ በዚሁ ቁጭት የአስተዳደር ቦርዱ መልአከ ሣህል አወቀን በድጋሚ ለመበቀል ሲል ሊያገኙ ተቃርቦ የነበረውን የመኖሪያ ፍቃድ እንዳያገኙና ከአሜሪካን አገር ጭምር እንዲወጡ የሚበረታታ የተንኮል ደብዳቤን ለኢምግሬሽን በመጻፉ ምክንያት የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት አቅም ባለው ሌላ ቤተ ክርስቲያን ጉዳያቸውን እንደገና መጀመር ግዴታ ሆኖባቸዋል፡፡ይህንኑ ጉዳያቸውን በርኅራሄ በማየትና በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳደደር ቦርዱ የጭካኔ አሠራር እጅግ በማዘን በአትላንታ የሚገኛው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ አስተዳደር የመኖሪያ ፈቃዳቸውን እንዲያገኙ እንደሚረዳቸውና በቂ ደመወዝ በመክፍል በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪነት እንዲያገለግሉ በደስታ ቀጥሮአቸዋል፡፡ ይህም ‹ እግዚአብሔርን ለሚያምኑና እንደ ሃሳቡ ለተጠሩት ነበር ሁሉለበጎ ነው፡፡ . የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት እንድናስታው የሚያደርግ ነው፡፡
ይህንኑ መልአከ ሣህል አወቀ በፈጣሪ ፈቃድ ያገኙትን መልካም ዕድልና እድገት የአርብ ጉባዔ በመንፈሳዊነት ደስታ ቢመለከተውም እኚህን የመሰለ ታላቅ አባት ከጉባዔው ላይ ማጣቱ ግን እጅግ አሳዝኖታል፡፡ በዚሁ ምክንያት መልአከ ሣህልንና ቤተሰባቸውን ለመሸኘት የአርቡ ጉባዔ ባለፈው ዓርብ ጥር 20 2003 ዓ.ም በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተገኙበት ልዩ መንፈሳዊ ጉባዔ በማዘጋጀት ደማቅ አሸኛኘት አድርጎላቸዋል፡፡በአሁኑም ሠዓት መልአከ ሣህልና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ንብረቶቻቸው አትላንታ በሰላም መድረሳቸው ተረጋግጦአል፡፡
በተጨማሪም የጉባኤው ዋና አስተባባሪና መምህር የሆኑት ቀሲስ መስፍንም ጉባዔው በተጠናከረ ሁኔታ ወደፊትም እንደሚቀጥልና በቅርቡም በፌብሩአሪ ወር መጨረሻ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ እንዲሚዘጋጅ ለሕዝቡ አስታውቀዋል፡፡ 
በአንጻሩም ደግሞ በመስክ ትምህርት ገበታ ላይ እያለ የዛፍ ቅርንጫፍ ግንድ የወደቀበት ታዳጊ ህጻን ማትያስ ብርሃኑም የአርባ ቀን መታሰቢያ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በተገኙበት በዚሁ የአርብ ጉባዔ ላይ በጸሎትና በዝማሬ እንዲሁም በዚሁ ዙሪያ ባተኮረ የወንጌል ትምህርት ታስቦ አምሽቷል፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት