Saturday, August 7, 2010



ነፋስም ወደ ፊታቸው ነበ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር እየተመላለሰ በሚያስተምርበት ጊዜ ልዩ ልዩ አስደናቂ ገቢረ ተአምራትን አድርጓል። ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በቅዱስ ቃሉ ፈውሷል። በባሕር ላይ በመሄድ ነፋሳትን በመገሰጽ በተፈጥሮ ላይ ያለውን ኃይል አሳይቷል። ምንም በሌለበት ምድረ በዳ ሁለት ዓሣና አምስት የገብስ እንጀራ አበርክቶ ከአምስት ሺህ ሰው በላይ እንዲመገብ አድርጓል። በልተው የተረፈ አሥራ ሁለት መሶብ ቅርጫት ተነስቷል። ይንን ያዩ እሥራኤላዊያን ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት የተናገሩለት መሲህ ይህ ነው በማለት ሊያነግሱት ፈልገው ነበር።
ዮሐ 6፥15


ንጉሰ ሰማይ ወምድር የሆነው ጌታ ሃሳባቸውን አውቆ ሕዝቡን አሰናብቷል። ሐዋርያትን በታንኳይቱ ወደ ፊት እንዲቀድሙት አድርጓል። እርሱም ለብቻው ወደ አንድ ተራራው ወጥቶ ጸልዮል። ይህም ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው። በምንሰራው መንፈሳዊ ሥራ እንዳንመጻደቅና ከውዳሴ ከንቱ ርቀን በጸሎት መትጋት እንዳለብን በገቢር ያስተማረን ትምህርት ነው። «ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤ ትሁት ነኝ እንዲል»። ማቴ 11፥28

ቀኑ እየጨለመ ጊዜውም እየመሸ ነው። ደቀ መዛሙርቱ የነበሩባት ታንኳ በባሕር መካከል ነበረች። ነፋስ ከፊት ለፊት ስለመጣ ታንኳይቱን መጓዝ ወዳለባት ወደ ቤተ ሳይዳ እንዳትሄድ አድርጓታል። ጌታ ግን ደቀ መዛሙርቱን በታንኳይቱ ላይ ሆነው እንዲሄዱ ያዘዛቸው ወደ ቤተ ሳይዳ ነው። ቤተ ሳይዳ ማለት የምህረት የቸርነት ቤት ማለት ነው። ታንኳይቱ ከፊት የገጠማት የነፋስ ኃይል ታንኳይቱን የሚፈታተንና በውስጥዋ የነበሩትን ደቀ መዛሙርቱን በጣም ያስጨነቀ ነበረ። የነፋሱን ኃይል ተቋቁማ ታንኳይቱ እንድትጓዝ ባላቸው ኃይል በጭንቅ ቢቀዝፉም ጉዞቸው በመከራና በፍርሃት የተሞላ ነበር።

የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጉዞን ከጀመረች ዘመናትን አስቆጥራለች። በዚህ ሰዎችን ያማዳን ረጅም ጉዞዋ በየዘመናቱ የተነሱ አላዊያን ነገስታት ከሐዲያንና መናፍቃን ብዙ ፈትና አድርሰውባታል። እርሷ ግን ፈተናውን ሁሉ ተቋቁማ ዛሬ ያለችበት ደረጃ ላይ ትገኛለች። ዛሬም በዚሁ ፈተና ውስጥ ገብታ ትታያለች። ወደፊትም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ይህ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ በዐውሎ ነፋስና በወጀብ ውስጥ እንዲሆን አድርጓታል።

የልጆቹን መጨነቅ የማይሻ ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ያለ መድኃኒአለም መጨነቃቸውን አይቶ በሌሊት ወደ እነርሱ በባሕር ላይ እየተራመደ መጣ። ምትሃት መሰላቸው። በንፋሱ ሲጨነቁ የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና በዚያ ሌሊት ፍርሃት በመካከላቸው ፍርሃት ነገሰ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን አጡ። ምንም እንኳን በውሃ ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መምጣቱ ከአእምሮ በላይ ቢሆንም ለእርሱ ግን «በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው»።

«አይዞችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ አላቸው።» ማር 6፥50 ፍርሃትን ማራቅ የሁል ጌዜ ተግባሩ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔር የፍርሃትን መንፈስ አልሰጠንም የፍቅርና ራስን የመግዛት መንፈስ እንጂ ማለቱ ይህን ቃል ያጸነዋል። 2ኛ ጢሞ 1፥7 በተለያየ ዘመን የተነሱ ሰማዕታት በየዘመኑ የተነሳውን የመከራ ዐውሎ ነፋስ የተቋቋሙትና ለክብር የበቁት የፍርሃት መንፈስ በውስጣቸው ስለሌለ ነው።

በሌሊት ጨለማ ባሕሩ ላይ የተነሳው የነፋስ ኃያል ከፍተኛ ስለነበር ታንኳይቱ ወደ ቤተ ሳይዳ የምታደርገውን ጉዞ አስቸጋሪ አድርጓታል። በውስጥዋም ያሉትን ደቀ መዛሙርት አስጨንቋል። ለሚሰራው ሥራ ጨለማና ሌሊት የማያግዱት ጌታ እነሆ ወደ ታንኳይቱ በዚያች ሌሊት ሲገባ ያ ሲያስጨንቃቸው የነበረው ነፋስ ጸጥ ብሎላቸዋል እነርሱም መረጋጋትና እፎይታን አግኝተዋል። እርሱ ባለበት ሕይወት ውስጥ ጭንቅ የለም። ይህን ያዩ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በጣም ተደንቀዋል።

ዛሬም እኛ በልዩ ልዩ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆነ ሕይወት ውስጥ እንገኛለን ወደ ድኅነት መንገድ የምትወስደን ታንኳይቱ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ነፋሳት ተከባ ትገኛለች። ማዕበሉ አስፈሪ ነፋሱም አስጨናቂ ቢሆንም እስካሁን ያለፈችው የፈተና ማዕበል አሁንም ታልፈዋለች። ያያዘችው እርፍ ሰማያዊና ወደ ኃላ የማያሰኝ በመሆኑ ጉዞዋን ትቀጥላለች። ደቀ መዛሙረቱ እንደዚህ አይነት ፈተና ሲገጥማቸው መፍትሄ ያደረጉት ከታንኳይቱ መውረድ አልነበረም። እዛው ታንኳይቱ ውስጥ እንዳሉ «ጌታ ሆይ እንዳንጠፋ አድነን» ብለው ጮሁ እርሱም ማዕበሉነና ነፋሱን ገሰጸ። ታላቅ ጸጥታም ሆነ። ማቴ 8፥27 እኛም ዛሬ ከልባችን ወደ እርሱ ልንጮህ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ ከፊት ለፊታችን የሚፈታተነንን ነፋስ በምህረቱ ያርቅልን። አሜን።!

1 comment:

  1. I think you have fine content but you could not address the fact that one of the Priest who was failed to execute the call he had received when he took the Priesthood. He had abandoned the children of God on the pulpit at St. Michael Church here in Dallas. And now he continues to perching against the Bible on the Church next door. Based on the Church Tewfik and kenona, he violated numbers of articles. Your blogs must risen up and speak. Let us see if your blog is a neutral if it posts this piece.


    Thanks,

    ReplyDelete

አስተያየት