Monday, January 25, 2010

ምርጫውን ለማስቆም ጀንበር ጠልቃለች ወይስ ገና ነች

የዕጩ አስተዳደር ቦርድ አባላት ምርጫ ውጤቱ እንደ ተሰማና የዶክተር ግርማ ደጋፊዎች ማሸነፋቸው እንደታወቀ በእነ አቶ ኢዩኤልና በደጋፊዎቻቸው የቦርድ አባላት መካከል ከፍተኛ መደናገጥና አለመረጋጋትን እንደፈጠረ በቅርብ የነበሩ እማኞች ገለጡ፡

በአንጻሩም ምርጫውን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሸነፍ ወላጅ ኮሚቴን ማእከል በማድረግ ጥሩ ዝግጅት ሲያደርጉ የሰነበቱት የዶክተር ግርማ ደጋፊዎችም ትናንት በፈንጠዝያ እንደዋሉና እንዳመሹም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ ኢዩኤልና ደጋፊዎቻቸው የቦርድ አባላት ምርጫው ትክክል አለመሆኑንና ዘዴ ተፈጥሮ መሰናከል እንዳለበት መላዎችን ሲያሰላስሉ ማደራቸውም ታውቋል፡፡ ይህ ካልሆነም ግን አቶ ኢዩኤል ነጋ መንበረ ሥልጣናቸውን በፈቃዳው እንደሚለቁ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

በምንም አይነት ንዑስ ኮሚቴ ውስጥ ገብተው ሳይሠሩንና ምንም አይነት የአገልግሎት ሪኮርድ ሳይኖራቸው ከእንጀራ ምጣዳቸው ላይ ተጠርተው ለቦርድ አባልነት የተመረጡት አቶ አበበ ጤፉ ወደ አስተዳደር ቦርድ እንዳይገቡ ለማገድና በዚሁ ሰበብ ምርጫው እንዲሠረዝ ለመድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የድሮውም ሆነ አዲሱ ባይሎ አንድ አባል ለአስተዳደር ቦርድ ምርጫ ለመቅረብና ለመወዳደር ቢያንስ አንድ አመት በንዑስ ኮሚቴ ማገልገል አንዳለበት እንደ አንድ መሥፈርት ያስቀምጣል፡፡

‹በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ ፡፡አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ፡፡ ›
እንደሚባለው ተረት የአስተዳደር ቦርዱ አቶ አበበ ገና በዕጩነት መጠቆማቸውን ስማቸው ሲደርሰው እዚያው ላይ መያዝና በዚህ መመዘኛ መሠረት ምርጫውን እንዳይወዳደሩ ማገድና ማስቀረት ይችል ነበር፡፡ ይህ ስህተት የአስመራጭ ኮሚቴውም የቦርዱም ስህተት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫውን በዚህ ሰበብ ታግሎ ለማሠረዝ እቺንም ታህል ምክንያት ማገኘታቸው ለአቶ ኢዩኤልና ደጋፊዎቻቸው መጽናኛ ነው ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

በሌላም በኩል ደግሞ እንደ እነ አቶ ጌታቸው ትርፌና መሰሎቹ የእነ ዶክተር ግርማና የደጋፊዎቻቸው ተመርጦ ወደ ቦርድ ውስጥ መግባት ለቤተክርስቲያናችን ትልቅ አደጋ አለው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ትናንት ጊዜ አገኘን ብለው ሌሎች አባላትን ከቤተክርስቲያን ለማበረርና ቦርድን ፈላጭ ቆራጭ ለማድረግ ሲሉ ከአሜሪካው ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ቅጂ አድረገው ያመጡት ሕግ ዛሬ እነሱኑ ከቦርድ ገፍትሮ አወጣቸው፡፡ ነገ ደግሞ ከአባልነት እንደሚያስወጣቸው አያጠራጥረም፡፡ በሠፈሩት ቁና ይሠፈርላችኋል ማለት ይህ ነው፡፡ ሰሚ ያላገኘው የሌሎችም ጩኸት ይህ እንዳይመጣ ነበር ፡፡ እንግዲህ ይቅመሱት፡፡ ይህ ገና የምጥ ጣር መጀመሪያ ነውና፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት