Thursday, January 14, 2010

የቦርድ ጠበቃ ማሳሰቢያ !

የክስ መጓተትና የይግባኝ ክስ መቀጠል የጠበቆች ፍላጎትና እንጀራቸውም እንደሆነ ይታወቃል፡፡በዚህ መሠረት የዳኛው ያልተጠበቀ ፍርድና ውሳኔ ትክክል ባለመሆኑ እኔንም በጣም አናዶኛል የሚለው የከሳሾች ጠበቃ ውሳኔው የኔንም ሪከርድ የሚያበላሽ ስለሆነ በራሴው ኪሣራ የይግባኝ ክሱን እቀጥላለሁ ብሎ ጉዳዩን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት ማቅረቡን ሰሞኑን መሰማቱ ይታወቃል፡፡

 የይግባኝ ክስ ደብዳቤ የደረሰው የቦርድ ጠበቃም የአስተዳደር ቦርዱ የይግባኝ ክስ እንደገና ስለመጣበት ይህንኑ ክስ ለመከላከል ከ80 000 ብር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ በመግልጹ በአስተዳደር ቦርድ አባላቱ መካከል ከፍተኛ መደናገጥና ቁጣን ፈጥሯል፡፡

ቀደም ሲል የአስተዳደር ቦርዱ ለዚሁ ክስ መከላከያ ከቤተክርስቲያኑ ያወጣው 49 000 ብርም ያለ ሕዝብ ፈቃድና ውሳኔ በመሆኑ በተጨማሪ ሊያስከስሳቸው እንደሚችልም አርድቷቸዋል፡፡

የአስተዳደር ቦርዱ በሽማሌዎች በኩል የቀረበውን የሽምግልና ጥያቄ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ቢቀበልና ልበሰፊ ሆኖ የከሳሾችንም ቅሬታ ሳይንቅ ቢያዳምጥና በመግባባት ሥራዎች ላይ ጥቂት ጊዜ ቢያጠፋ ኖሮ በስንት ድካምና ጥረት የተሰበሰበው የቤተክርስቲያኒቱ ገንዘብ እሳት የጋባ ቅቤ አይሆንም ነበር ፡፡ አሁንም ይህንኑ ለማድረግ ገና ጀንበር አዘቀዘቀች እንጂ ጨርሶውኑ አልጠለቀችም፡፡

እስካሁንም ከከሳሾች ኪስና ከቤተክርስቲያኒቱ ካዝና የወጣውና ጠበቆች ኪስ የገባው ገንዘብ በድምሩ ከ 80 000 ብር በላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡መፍትሄን በነጻ ማምጣት ሲቻል የእግዚአብሔርና የምእመናን ገንዘብ ያለአግባብ ማባከን ከቁማር ጫወታ ተለይቶ የሚታይ አይደለምና በእግዚአብሔርም በሰውም ዘንድ ያስጠይቃል፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት