Wednesday, April 27, 2011

ሰሙነ ፋሲካ !

ይ.ካ. ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን 
 Christ rose from the dead
ይ.ሕ. በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን
By great power and authority
ይ.ካ. አሠሮ ለሰይጣን
Christ bound Satan
ይ.ሕ. አግአዞ ለአዳም
Christ set Adam free
ይ.ካ. ሰላም .Peace
ይ.ሕ. እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሓ ወሰላም። 
.From now becomes happiness 
And peace



ካለፈው እሁድ ሚያዝያ ፲፮/፪ሺ፫/ዓ/ም ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤእሁድ ሚያዝያ ፳፫ /፪ሺ፫/ዓ/ም ድረስ ሰሙነ ፋሲካ ይባላል።
ፋሲካ - ማለት መሸጋገርያ ፣ ድልድይ ማለት ነው። (በግዕዙ - ዐዲው ፣ ዕድወት ፣ ማዕዶት ይላል) ጥቅስ. <<ፋሲካ ብሂል ፤ በዘቦቱ አዶነ እሞት ውስተ ሕይወት>>
ፋሲካ - ማለት አለፈ ማለት ነው። የእስራኤል ልጆች በግብጽ አገር በግ አርደው ደሙን በደጃፋቸው በመርጨት ከእግዚአብሔር ቊጣ ዳኑ። የእግዚአብሔር መልአክ በዚያች ሌሊት ግብጻውያንን ሲቀሥፍ ደም በነበረበት አልፎ ስላልገደለ ወይም ደም የተረጨበትን ቤት ስላለፈ ቀኑ ፋሲካ ተባለ። እንደዚሁም ለፋሲካ የሚታረደው በግ ፋሲካ ይባላል። ኦሪት ዘፀአት ፲፪ ፡ ፩-፲፫ ፤ (12 ፡ 13)
በየዓመቱ በግ እያረዱ የእስራኤል ልጆች በመጀመርያ ወራቸው በ፲፬ኛው ቀን የፋሲካን በዓል ያከብራሉ።
ከዚያም ምሽት እስከ አንድ ሳምንት ድረስ የቦካውን ነገር ለመብላት ስላልተፈቀደላቸው የሙሉ ሳምንት በዓል የቂጣ በዓል ተባለ። የቂጣ እንጀራ መብላት የእስራኤል ልጆች በችኰላ ከግብጽ እንደ ወጡ የመታሰቢያ ምልክት ነው። ዘፀአት ፲፪ ፡ ፲፰-፳ ፣ ቊ ፴፫-፴፭። ዘዳግ. ፲፮ ፡ ፩-፫
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ሳምንት የአይሁድ የፋሲካ ሳምንት ነበር።
ማቴ ፳፮ ፡፲፯-፳፭። ሉቃ ፳፪ ፡ ፯-፲፮። ዮሐ ፲፰ ፡ ፴፰-፵።
ንጹሕ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ደሙን ስላፈሰሰልን <<ፋሲካችን ክርስቶስ>> ተባለ።
፩ኛቆር. ፭ ፡ ፯። ፩ኛጴጥ. ፩ ፡ ፲፰-፲፱።
ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ = በዓለ ፋሲካ ተብሎ ይጠራል።
አይሁድ ምንም እንኳ ጌታ በየጊዜው ያደርገው በነበር ልዩ ልዩ አምላካዊ ተአምራት ቅናት ምቀኝነት አድሮባቸው በማመስገን ፈንታ ክፉ ቢመክሩበትም ጊዜው ስላልደራሰ አልተሳካላቸውም ነበር። ጌታ ፈቃዱ ሆኖ የሚሰቀልበትን ጊዜ እንደ ደረሰ አውቆ የሰላማዊ ዘመን ምሳሌ የሆነ አህያን ተጭኖ ከደብረ ዘይት በብዙ ሺህ ሕዝብ ታጅቦ ኢየሩሳሌም ከተማ ገብቶ እስከዚያ ድረስ የዳዊት ልጅ ሲባል ቆይቶ ለዳዊት ልጅ በሰማይ መድኃኒት መባል ይገባዋል እየተባለ ከዳዊት ባሕርይ የነሳው ሥጋ አምላክነቱን ከገለጠ በኋላ አይሁድ በቅናት እሳት ተቃጥለው እርስ በርሳቸው የምናገኘው ረብህ ጥቅም እንደሌለ አታውቁምን ይህ ማለት ከእንግዲህ ወዲህ ዞር ብሎ የሚያየን ሰው የለም ማለታቸው ነው። <<ናሁ ኵሉ ዓለም ተለወ ድኅሬሁ>> እነሆ ዓለም ሁሉ ተከተለው (ሰው ሁሉ አመነበት አሉ)። ዮሐ. ፲፪ ፡ ፲፱-፳
ከዚህ በኋላ እንያዘው እንግደለው የሚል ክፉ ምክራቸውንና አድማቸውን ያጠኑ ጀመር። ስለዚህም ሰኞ መጋቢት ፳፫ ቀን የሆሣዕና ማግስት ለምክክር ተሰበሰቡ ከጥዋት እስከ ማታ ሲመካከሩ ሲፋጁ ውለው ሳይሳካላቸው ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ ተበተኑ።
እንደገና በማግስቱ ማክሰኞ መጋቢት ፳፬ ቀን እንደዚሁ ተሰብስበው ሲማከሩ ከዋሉ በኋላ ሳይሳካላቸው ቀረ።
እንደዚሁም ደግሞ ረቡዕ መጋቢት ፳፭ ቀን እንደገና ተጠናክረው ምክራቸውን ጀመሩ፤ በዚሁ ቀን ከደቀመዛሙርቱ አንዱ ይሁዳ አስቆረታዊ የሚባል በገንዘብ ፍቅር ተቃጥሎ በጥዋቱ ገና ፀሐይ ሳይወጣ ተነሥቶ ጌታችንና ወንድሞቹ ሐዋርያትን በደብረ ዘይት ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የካህናት አለቆችንና የኦሪቱን መምህራን እንዲህ አላቸው ፤ መሲሕ የሚሉት ኢየሱስን አሳልፌ ብሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ ? እንደፈለጋችሁ ታደርጉት ዘንድ እኔ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ ፤ የምትሰጡኝን ንገሩኝ ፤ ቀድሞም ትይዙት ዘንድ እንደምትፈልጉ እኔ አውቃለሁ ፤ እርሱ ግን ስለ ክፉ ሥራው ከእናንተ ይሠወር ነበር አላቸው።
በቤተ መቅደስ ውስጥ ለክፉ ሥራ አንድነት የተሰበሰቡ ፡ ስማቸው የቀያፋ አማት ሐና ፡ ጸሐፊው ሲናን ፡ ዮድና ፡ ሚልክያስ ፡ አርማንየስ እለእስክንድሮስ የተባሉት የካህናት አለቆች የምንወድህ ወንድማችን ይሁዳ ሆይ መልካም አደረግህ ፤ መልካም የምሥራችም አበሠርከን ፤ በዚህ በምትነግረን ነገርም ሁላችንም ደስ ብሎናል ፤ በቤት ጥላ ውስጥም በመስኮትም ቢሠወር ፡ እርሱን ብታስይዘን የምትሻውን ሁሉ ካለው ብር እንሰጥሃለን አሉት።
የሕግ ጸሐፊ ሲናንም ይሁዳን አንተ የርሱ ደቀ መዝሙሩ እንደሆንክ እኛ እናይሃለን ፤ ተመልሰህ እንዳትከዳን እንጃ ፡ አለው።
ይሁዳም ሁሉን የያዘ ፈጣሪ የተመሰገነ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ በእውነት እርግጡን ተናገርኩ ፤ አሳልፌም እሰጣችኋለሁ ፤ ካላመናችሁም ከእናንተ አንዱ ከእኔ ጋራ ይምጣ ፤ ከደቀመዛሙርቱ ጋራ ያለበትንም አሳየዋለሁ አላቸው።ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው። ሠላሳ ብር ሊሰጡት ተስማሙ እሱም በስውር አሳልፎ ሊሰጣቸው ወደደ።
ስለዚህ በይሁዳ መገኘት ረቡዕ ዕለት ምክራቸው ተሳክቶላቸው አደረ።
በማግስቱ ሐሙስ መጋቢት ፳፮ ቀን ዛሬ እንስቀለው ብለው አሰቡ። ነገር ግን የፋሲካ በዓላቸው ስለሆነ ሕዝቡ ያውከናል በማለት ለነገ ዐርብ ይሁንልን በማለት ተስማምተው አደሩ።
ማቴ ፳፮ ቁ ፫ ሉቃ ፳፪ ቁ ፩-፯
ጌታ የጸሎተ ሐሙስ ዕለት በወዳጁ በአልአዛር ቤት በተቀመጠ ጊዜ መሥዋዕተ ኦሪትን ሽሮ መሥዋዕተ ወንጌልን ሾመላቸው ፤ ምሥጢረ ቊርባንን አሳያቸው።
“ኅብስቱንም አንስቶ ነገ አይሁድ የሚቆርሱት የሚፈትቱት ሥጋዬ ይህ ነው ፤ ኃጢአታችሁን ያሥተሰርይላችሁ ዘንድ ንሡ ብሉ ብሎ ሰጣቸው።
ጽዋውንም ሲሰጣቸው ነገ አይሁድ የሚቀዱት የሚያፈሱት ደሜ ይህ ነው ፤ ኃጢአታችሁን ያሥተሰርይላችሁ ዘንድ ንሡ ጠጡ ብሎ ሰጣቸው።”
መሥዋዕተ ኦሪት ምንድን ነበር ብንል ? ሜል ፣ ገች ፣ በግ ይሠዉ ነበር ያንን አስቀረው ማለት ነው።
ጌታ ለሐዋርያት ምስጢረ ቁርባንን ካሳያቸው በኋላ ሥርዓተ ጸሎትን ለማሳየት ወደ ጌቴሴማኒ ወጣ። ከዚያም ደርሶ የቀሩትን በዚያ እስክ ጸልይ ድራስ እዚህ ቆዩ ብሎ ሦስቱን ጴጥሮስ ዮሐንስ ያዕቆብን ይዞ ሰውነቴ እስከሞት ደርሳ አዘነች እያለ ያዝን ይተክዝ ጀመር። እንደዚሁም ከኔ ጋራ እንደ እኔ ተግታችሁ ጸልዩ ብሎአቸው ድንጋይ ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ከሶስቱ ተለይቶ በቀዊም ፣ በሰጊድ ፣ በአስተብርኮ ፣ በሰፊሐ አእዳው ፣ ወዙ በዝቶ እስኪወርድ ድረስ መላልሶ ጸለየ።
ስለምን ጌታ ጸለየ ብንል?
ለኛ አብነት ለመሆን እንዲህ እያዘናችሁ እየተከዛችሁ በሰጊድ ፣ በአስተብርኮ ፣ በሰፊሐ አእዳው ፣ ወዛችሁ በዝቶ እስኪወርድ ድረስ መላልሳችሁ ብትጸልዩ ትጠቀማላችሁ ሲለን ነው።
ከዚህ በኋላ ወደ ደቀመዛሙርቱ ተመልሶ ተኝተው አገኛቸውና ጴጥሮስን እንዲህ አለው ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት እንኳ መትጋት ተሳናችሁ? አሁንም ወደ ኃጢአት ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ ብሎ ተግቶና መላልሶ መጸለይ እንደሚገባ አስተማራቸው።
ደግምሞ ሦስት ጊዜ እየተመላለሰ ጸለየ ይህ ሁሉ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሆን ፍጻሜው እስከ ምጽአት ለምንነሳው ለኛ አብነት ለመሆን ነው። ማቴ ፳፮ ቁ ፵-፵፮
ከዚህ በኋላ ተመልሶ እንግዲህስ ተኙ እረፉ በኃጥኡ እጅ የምያዝበት ጊዜ ደረሰ አላቸው።
ሐሙስ መጋቢት ፳፮ ከምሸቱ ሶስት ሰዓት ሲሆን ይሁዳ ከሊቀ ካህናቱ ጋር እና ከፈሪሳዊያን ፤ ሰጲራ የሚባል የአራት ቤት ጭፍራ ይዞ እንዲሁም ሌሎች ረዳቶች አክሎ (ጨምሮ) መጣ።ይህን ያደረገበት ምክንያት ጌታችን ብዙ ሕዝብ ይከተለው ነበርና ድንገት ጠብ የተነሳ እንደሆነ በማለት ነው። ተጨማሪ ወታደሮች ጲላጦስ ዘንድ ሄዶ አመጣ። ጊዜው ጨለማ በመሆኑ ፋኖስ የችቦ መብራት ይዘው የጦር መሳሪያ ሾተል ጎመድ ይዘው ይሁዳ በፊት በፊት እየመራቸው ደርሰው የጌታን ፊት ለይተው ስለማያውቁት ይሁዳ እኔ ሰላም የምለውን ያዙ ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ስለነበር ወደ ጌታ ቀርቦ << በሀ ረቢ>> መምህር ቢሰኛህን ጥለኛህን አያውለው አያሳድረው ብሎ እጅ ነሳው። ይህ ማለት ከሱ የበለጠ ሌላ ጠላት ኖሮ ሳይሆን ራሱን አያውለኝ አያሳድረኝ ብሎ መራገሙ ነው። ጌታም ወዳጄ ልታስይዘኝ መጣህን? አለው ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ <<መነ ተኀሥሡ>> ማንን ትሻላችሁ አላቸው። እነሱም መልሰው <<ኢየሱስሃ ናዝራዌ ነኀሥሥ>> የናዝሬቱ ኢየሱስን እንሻለን አሉት። ጌታ ኢየሱስም እኔ ነኝ አላቸው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደኋላቸው ተመልሰው ወደቁ። ወደ ኋላም የወደቁበት ምክንያት በኋላ የሚጠብቃቸው ኩነኔ እንዳለ ለማስረዳት ነው። በእጃቸው የያዙት ጦር ሾተል ጎመድ ሁሉ ከእጃቸው እየለቀቀ ጌታችን እግር ሥራ ዘንድ ሄዶ ሰገደለት። ይህም የሆነበት ምክንያት ፈጣሪነቱን ለመግለጽ ነው። እንደዚሁም ጌታ በተቀደሰው ፈቃዱ ማለት በገዛ ፈቀዱ ተያዘ እንጂ አይሁድ በኃይላቸው ወይም በጦር መሣሪያቸው እንዳልያዙት ለማስረዳት ነው። ደግሞም ሁለተኛ ጠየቃቸው <<መነ ተኀሥሡ>> ማንን ትሻላችሁ? አላቸው <<ኢየሱስሃ ናዝራዌ ነኀሥሥ>>የናዝሬቱ ኢየሱስን እንሻለን አሉት። እኔ ነኝ አላቸው። እንደበፊቱ ወደኋላቸው ተመልሰው ወደቁ።
እንደዚሁም ደግሞ ለሶስተኛ ጊዜ <<መነ ተኀሥሡ>> ማንን ትሻላችሁ? አላቸው <<ኢየሱስሃ ናዝራዌ ነኀሥሥ>>የናዝሬቱ ኢየሱስን እንሻለን አሉት። እኔ ነኝ አላቸው። እንደበፊቱ ወደኋላቸው ተመልሰው ወደቁ። ለምን ሶስት ጊዜ ጠየቃቸው ብንል ምንም በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት በዚህ ተወስኜ ብታዩኝ በአንድነት በሶስትነት ስሠለሥ ስቀድስ የምኖር የባሕርይ አምላክ ነኝ ማለቱ ነው። ከዚህ በኋላ የምትሹ እኔን ከሆነስ እኒህን ተዋቸውና ይሂዱ ብሎ ሐዋርያትን አሰናብቶ በገዛ ፈቃዱ ተያዘ። ዮሐንስ ፲፰ ፡ ፬-፱
አይሁድም ተነባብረው ይዘው አስረው እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት ከዚያም እንደታሰረ ወስደው ለጲላጦስ ሰጡት ሶስት ሰዓት ሲሆን አጥንቱ እስኪታይ ድረስ ገረፉት በዚህ ጊዜ ለተሳልቆ ቀይ ግምጃ አለበሱት የእሾህ ዘውድ ጎንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት በቀኝ እጁ ዘንግ አስያዙት። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ቢሰኛህን ጠበኛህን አያውለው አያሳድረው እያሉ ብፍና ተሳልቆ ሰገዱለት ፤ ፊቱን ጸፉት ጽሕሙን ነጩት በዓይኑ በጆሮው በአፍንጫው ደሙ እስኪጎርፍ ድረስ ተናገር የመታህ ማነው? እያሉ በዘንግ ራስ ራሱን ደበደቡት እንዲህ አድርገው ከተዘባበቱበት በኋላ ያለበሱትን ልብስ ገፈው የሚሰቀልበትን መስቀል አሸክመው እያዳፉና እየገፉ ወደ ሚሰቀልበት ቀራንዮ ወሰዱት በዚያ ትንሽ ጨርቅ እንኳ ሳያስታጥቁ ራቁቱን የጎኑ አጥንት እስኪታይና አንድ ሁለት ተብሎ አስኪቆጠር ድረስ በሰባት ክንድ እንጨት ላይ ስበው በአምስት ችንካር ቸነከሩት። ዮሐ ፲፰ ፡ ፱-ፍጻሜ። ማቴ ፳፯ ፡ ፩-ፍጻሜ
ቀትር ሲሆን <<ዘኢጾረ መስቀለ ሞትየ>> ብሎ በቃል ያስተማረውን በግብር ለመፈጸም ዐርብ መጋቢት ፳፯ ቀን ከቀኑ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ። በዚህ ጊዜ ፀሐይ ከብርሃን ተለየ ማለት ጨለመ ማብራቱን ተወ ፤ ጨረቃ ደም ሆነ (መሰለ) ፤ ከዋክብት ወደቁ ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ ፤ ምድር ተናወጠ (መርገመ ሥጋ ጠፋ)፤ ዓለቶች ተሰነጠቁ (መርገመ ነፍስ ጠፋ)፤ መቃብራት ተከፈቱ (ሙስና መቃብር ጠፋ)፤
ውሀ ጠማኝ ቢላቸው ሀሞት የተቀላቀለበት መራራ አጠጡት ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን <<የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ አትፍረድባቸው>> ብሎ በገዛ ፈቃዱ ቅድስት ነፍሱን ከክቡር ሥጋው ለየ። ወዲያውም መለኮት በአካለ ነፍስ ሲኦል ወርዶ ከአዳም እስከዚያ ድረስ የወረዱትን ነፍሳት አውጥቶ ገነት አገባቸው። ማቴ ፳፯ ፡ ፶፩።
<<ወሖረ ኀበ እለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ>> ነፍሳቸው ታስራ ትኖርበት ወደ ነበረው ሲኦል ወርዶ ነፃነትን ሰበከላቸው (አወጀላቸው)። ፩ጴጥ ፫ ፡ ፲፱።
<<እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሠቱ>> በሲኦል ውስጥ ያላቸሁ ውጡ ፤ በጨለማ ውስጥ ያላችሁ ተገለጡ አላቸው።
አዳምና ሔዋን ከገነት የወጡበት ቀን ዓርብ ነበር ፤ ሰዓቱም ሠርክ ነበር። ልክ በወጡበት ቀንና ሰዓት ተመልሰው ገቡ።
ስለዚህ ዓርብ ዕለት ጥንቱንም አዳም የተፈጠረባት የፍጥረት መካተቻ ፤ አዳም ከገነት የወጣባት ነበረች።
አሁንም አዳም የዳነባት ነፍሳት ከሲኦል ወጥተው ወደ ቀድሞ ርስታቸው ገነት የገቡባት የድኅነተ ዓለም መሠረት ጥንተ መድኃኒት ስለሆነች በዚህች ዕለት ነገረ መስቀሉን እያሰብን በስግደት በጸሎት ውለን ፤ ሠርክ ሲሆን <<ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ>> በማለት ከበሮአችንን አንሥተን ጸናጽላችንን ይዘን ተድላ ደስታችንን እንገልጻለን።
ከነቢይ ዳዊት ጋር ሆነን <<በዘመናችን ሁለ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን። መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፈንታ ደስ ይለናል>>። እያልን ታዲጊያችን ክርስቶስን እናመሰግነዋለን። መዝሙር ፹፱ ፡ ፲፭
ከዚህ በኋላ አንድ ለንጊኖስ የሚባል ወታደር አለን ሞተ ? ብሎ በተሳለ ጦር ቀኝ ጎኑን ቢወጋው ትኩስ ደም ለቁርባናችን ጥሩ ውሀ ለጥምቀታችን እንደ <<ለ>> ፊደል ሆነው ፈሰሱ። ይህም የሥጋ አምላክነትና የአራቱን ባሕርያት አለመለያየትን ያስረዳል።
<<ወተክዕወ ደመ መሢሑ ለአብ ወማይ ዘውኅዘ እምገቦ መሢሑ ተክዕወ ላዕለ አዳም ወአጥመቆ ከመ ያብኦ ውስተ ዓቢይ ክርስትያን>> እንዳለ መጽሐፈ ምስጢር። ለንጊኖስም አንድ ዓይና ነበርና ከደሙ ተፈናጥቆ ቢነካው ዓይኑ በራለት።
ከዚህም በኋላ በሠርክ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የሚባሉ የጌታችን ወዳጆች ነበሩና መጥተው ጲላጦስ ጌታችንን ስጠን አውርደን እንቅበረው አሉት። ማቴ ፳፯ ፡ ፶፱-፷፮።
ጲላጦስም አውርዳችሁ ቅበሩት አላቸው። ዮሴፍ ድርብ በፍታ ፤ ኒቆዲሞስ የመቶ ወቄት ሽቶ አምጥተው ችንካሩን እየነቀሉ ከመስቀሉ አውርደው ሽቶውን በበፍታው ላይ ረብርበው ሲገንዙት። ዓይኑን ግልጥ አድርጎ ቢያያቸው እንደ ሻሽ ተነጠፉ እንደ ቅጠል ረገፉ በግንባራቸው ተደፉ።
አቤቱ ጌታችን ሆይ ምን አደረግን አሉት ምነው እናንተስ እሩቅ ብእሲ ይመስል ዝም ብላችሁ ትገንዙኝላችሁ አላቸው። አቤቱ ጌታችን ሆይ ምን አያልን እንገንዝህ አሉት።
ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ። አቤቱ ይቅር በለን።
ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት በዮርዳኖስ የተጠመቀ በመስቀል ላይ የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን እያላችሁ ገንዙኝ አላቸው።
መጽሐፈ ኪዳንን ሲጀምርላቸው ሲያስተምራቸው ነው። እንዲህ እያሉ እንደ ሥርዓታቸው በሚገባ አድርገው አጥበው ገነዙት።
ዮሴፍም ለራሱ ብሎ ያሳነጸው ሐዲስ መቃብር ነበርና ከዚያ ወስደው ቀበሩት። ታላቅ ድንጋይ አጋላብጠው መቃብሩን ገጥመውት ሄዱ። ወዲያውኑ ከዚያ እንደ ሄዱ ለወዳጆቹ ለ፲፪ ሐዋርያት ለ፸፪ አርድእት ለ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት እስከ ፫ ቀን እነሣላችኋለሁ እዘኑ አልቅሱ እህል ውሀ አትቅመሱ በሏቸው ብሎ አዞናል ብለው ነገሯቸው።
በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓቱን በሚገባ ጠብቃ በየዓመቱ የቅዳሜ ሥዑር ቀን ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ቃጤማና ቃጭል ይዘው በየምዕመናኑ ቤት እየዞሩ ልክ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንዳደረጉት የምሥራች << ነፍሳት ከሲኦል ወጡ ፤ ርስተ ገነት ተመለሰችልን ፤ አባታችን አዳም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት የተድላ ደስታ ምልክት ወይም መግለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቃጤማ ይዘው ምእመናንን ያበሥራሉ። የቅዳሜ ሥዑር ሥነ ሥርዓት በዚህ አብቅቶ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፫ መዓልት ፫ ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በኅቱም ድንግልና እንደ ተወለደ በኅቱም መቃብር ከሙታን ተለይቶ ከሙታን ተቀድሞ በዘመነ ማርቆስ መጋቢት ፳፱ ቀን እሑድ ከሌሊቱ ባ፲ ሰዓት ተነሣ ። << እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ>> መዝሙረ ዳዊት ፸፯ ፡ ፷፭። ማቴ ፳፰ ፡ ፩ ፤ ማር ፲፮ ፡ ፩ ፤ ሉቃ ፳፬ ፡ ፩ ፤
ዮሐ ፳፩፡፩ ተነሥቶም በመጀመርያ ለማርያም መግደላዊት ቀጥሎ ለ፲፪ቱ ሐዋርያት በሌላ ቀን ደግሞ ለሦስቱ ለአራቱ ደቀ መዛሙርቱ ተገለጸላቸው ከነሱም ጋር በላ ጠጣ መጽሐፈ ኪዳንን ኢያስተማራቸው ፵ ቀን በምድር ቆየ ልክ በተነሣ ባርባኛው ቀን በክብር በይባቤ ወደ ሰማይ ዐረገ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment

አስተያየት