Friday, November 26, 2010

ክራባት ! የሰላዩ ብዕር 
ረዳት ካሜራ
ክፍል ሦስት
እኔም በበኩሌ የባለቤቴ ጠባይ ባልተጠበቀ ሁኔታ መለወጥና በትዳራችን መካከል የነበረው ጣዕም ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ መምጣት እጅግ በጣም አሳስቦኝ ነበር ፡፡ እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ ከእርሷ ጋር ለመኖር ወስኜና ወድጃት ያገባኋት የትዳር ጓደኛዬን ከምንም በላይ እወዳታለሁ፡፡እርሷ ስሜታዊ ሆና በየምክንያቱ ብትበሳጭም ብስጭቷን የሚያበርድ እንጂ ንዴቷን የሚጨምር ሥራ ሠራሁ የምለው በእኔ በኩል አንዳች ነገር የለም፡፡እሷን የሚያስቀይም መጭፎ ነገር ማደረጌም ጨርሶ ትዝ አይለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለምታሳየኝ አክብሮት ለሌለው ሥነ ምግባሯ ቂም ይዤ ወይም እርሷን በክፉ ለመበቀል በጭራሽ አልሜም አስቤ አላውቅም፡፡የእኔ የሁሉ ጊዜ ምኞት እርሷ በአእምሮዋ ታድሳና ተለውጣ ማየት ነው፡፡ ወዲያው መልሳ ብትረሳውም ከእርሷ ያየሁትና የምወድላት መልካም ነገር ቢኖር ካጠፋች በኋላ የምታደርገው ጸጸት ነው፡፡ ያ እንዳልሰለቻትና እንዳልጠላት አድርጎኛል፡፡

ተፈጥሮአዊ ባህሬዬ ሆኖ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ማስታወሻ መዝግቦ መያዝ ስለምወድ የየእለቱን ክስተቶች ሁሉ አመዘግባለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት በቁጥር በርከት ያሉ ባለ ገጸ ብዙ የማስታወሻ ደብሮቼ የመጽሐፍ መደርደያዎቼን አጣበውታል፡፡ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና ማስታወሻ የምጥፍበት ብዕር ዛሬ ጥበብ ተጨምሮለት ባለቪዲዮ መቅረጫ ብዕር በመሆኑ ብዙ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ረድቶኛል፡፡አንድ ቀን ሊጠቅም ይችላል በማለት እርሷ በቤት ውስጥ ስትናደድ የምታደርጋቸውን ድርጊቶች በሙሉ ረቀቅ ባለና እርሷ በማታውቀው መንገድ እየቀዳሁ አስቀምጣለሁ፡፡ብዙ ጊዜ ከምለብሳቸው ኮቶቼ ደረት ኪስ የማይለየው ሰላዩ ብእር በእርሷ ዘንድ የሚታወቀው አለባበስ ለማሳመር (ለጌጥ) ወይንም ማስታወሻ በወረቅት ላይ ለመጻፍ የሚያዝ ነው እንጂ የሚመስላት ሌላ አገልግሎት እንዳለው አስባም ጠርጥራም አታውቀም፡፡ብዙ የመረጃ ሰው ስላልሆነች አብዛኛውን አዳዲስ ክስተትና የቴክኖሎጂውን ፈጠራ የምትሰማው ከሜዲያው ይልቅ ከእኔ ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ምናልባት ከጠየቀችኝ እነግራታለሁ ብዬ እስካሁን ግን የሰላዩን ብእር የካሜራ ጥበብ አልነገራኳትም፡፡ ስትናደድና ቁጣ ስትጀምር ጠጋ ብዬ በሰከነ መንፈስ የማነጋገርና በፊት ለፊቷ ሆኜ የማረጋጋት ልማድ ስለነበረኝ ያሉትን ሁኔታዎች ሁሉ በድምጽና በምስል በመቅረጽ በዚህ መልኩ በርከት ያሉ መረጃዎችን አሰባስቤአለሁ፡፡


ሌላውና የሚያስገርመው ነገር የሰላዩ ብእር ተለዋጭ ረዳት ካሜራ ክራባቴ መሆኑ ነው፡፡ ገና ስንተዋወቅንና ፍቅር ስንጀምር ባለቤቴ ሱፍ ስለብስ በተለይም በሸሚዝና በክራባት ስሆን አለባበሴ እጅግ እንደሚያስደስታት ስለነገረችኝ እርሱዋን ለማስደሰት ስል ይህን የፕሮቶኮል አለባባስ አዘወትራለሁ፡፡በዚህ ምክንያት ያሉኝ ክራባቶች ሁሉ እጅግ ውድና አንዳንዶቹ በቴክኖሎጂው ረቂቅና ዘመናዊ የቪዲዮ ካሜራ የተገጠመላቸው ናቸው፡፡
ይህ የክራባት ካሜራ እስከ 4 ሰዓታት ያሀል የመቅረጽ ችሎታ ያለው ሲሆን በላ 4 GB ሰው ሰራሽ ፈጣን አእምሮ ( Flash Memory ) የተገጠመለት ነው፡፡ እንደ ሰላዩ ብዕር ሁሉ የቀረጸውን የድምጽና የቪዲዮ ምስል በቀላሉ ወደ ማንኛውም ኮምፒውተር ማስተላለፊያ መሳሪያዎች ያሉት ካሜራ አዘል ክራባት ነው፡ካበለቤቴ ጋር ለነበረን ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ሁሉ የክራባት ካሜራዬ ያሉትን ሁኔታዎች በመቅረጽ ብዙ ተባብሮኛል፡፡ 


ይህም ብቻ ሳይሆን በመኝታቤት አልጋችን ትይዩ ባለው Dressing Table ላይ የተቀመጠውም የጠረቤዛ ሰዓት ቴክኖሎጂው በገጠመለት ሥውር የቪዲዮ ካሜራ መቅረጫው በመካከላችን ያለውን ጤናማ ያልሆነ ንግግር በመቅረጽና በመቅዳት እርሱም እንዲሁ ትብብር አድርጎልኛል፡፡እርሷ ገና መነጫነጭ ስትጀምር እኔ የጧት ሥራ መንቂያ ሰዐቱን እንደሚሞላ ሆኜ የመቅጂያውን በተን እጫነውና እንደመርፌ ቀዳዳ ያለች የካሜራውን ቀዳዳ አስተካክዬ አስቀምጠዋለሁ፡፡ እርሱም ባትሪው ከተሞላ ለ12 ሰዓታት ያህል የመቅረጽ አቅም ያለው ስለሆነ እስከ ማቆመው ድርስ የታዘዘውንና የተሠጠውን ሥራ ይሠራል፡፡ 


በዚህ መልኩ የባለቤቴን አላስፈላጊ ጠባዮችንና ድርጊቶች በመረጃ መልክ ከሰበሰብኩ በኋላ በርከት ላሉ ቀናት ከራሴ ጋር ባደረኳቸው ተደጋጋሚ ስብሰባዎችና ውይይቶች በፍቅርና ቀልድ መልክ በልዩ ሁኔታ ለእርሷ ማሳየትና ማስተማር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ይሁን እንጂ በጉዳዩ ሠይጣን በመካከል እንዳይገባና ነገሩን ሁሉ እንዳያበላሸው፤ እግዚአብሔርም እንዲረዳኝ፤ ይህን ያሰብኩትን ጉዳይ ለበጎ እንዲያደርግና እርሷን ለማስተማር እንዲጠቀምበት አጥብቄ ጸለይኩ፡፡በሕይወቴ ዘመን ሁሉ መልካም እያደረገልኝ እዚህ ያደረሰኝ አምላኬ በእርሷ ባሕርዪ በኩል የገጠመኝን ይህን ፈተና በድል እንድወጣው እንደሚረዳኝም አልተጠራጠርኩም፡፡


ከላይ በክፍል ሁለት መጨረሻ ባለቤቴ ለመግለጽ እንደሞከረችው እርሷን ከምንጊዜውም የበለጠ ለማስደስትና 5ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችንን በጥሩ ሁኔታ ለማክበር ወደ ዝነኛው Rennasiance Hotel በመጓዝ እዚያ 4፡00pm ላይ ደረስን፡፡ ለሁለት ቀናት የምንለብሳቸውን ልብሶችና የሚያስፈልጉንን እቃዎች ሁሉ የያዝንበትን መለስተኛ ሻንጣ በአንድ እጄ የባለቤቴን ግራ እጅ ደግሞ በቀኝ እጄ ይዜ ልቤ ፈራ ተባ እያለ ወደ ክፍላችን መውጫ Eleveter አመራን፡፡የፈራሁት ካሁን ካሁን እጄን ከእጇ ላይ ወርውራ ታዋርደኛለች ብዬ ነበር ፤ እግዜር ይስጣት ክፍላችን በር ላይ እስክንደርስናና እኔም በሩን ለመክፈት እጇን በፈቀዴ እስከለቀኩበት ሰዓት ድረስ አንዳች የቃውሞ ምልክት አላሳየችም፡፡ ልቤን በጣም ደስ አለው፡፡


ገና ከበር እንደገባን በነጭ ጨርቅ ሐር ልብስ የተሸለመች ትንሽ ክብ ጠረቤዛ ላይ ቀያይ ገና የፈነዱ የጽጌረዳ አበቦች አንጸባራቂ በሆነ የአበባ ማስቀመጫ ተቀምጠዋል፡፡ በመኝታው አልጋ ራስጌ ባለው ግድግዳ ላይ የሚያምርና እርሷም በጣም ትወደው የነበረ የሠርጋችን ፎቶ ግራፍ ዋጋው ውድ በሆነ ትልቅ ፍሬም ሆኖ ተሰቅሏል፡፡የሁለታችንም ስም ያለበት Happy 5Th Year anniverssary From Rennasiance Hotel mannger የሚል ጽሑፍ ያው ፖሰት ካርድ ከመኝታው አልጋ የቀኝ ኮመዲኖ ተቀምጧል፡፡ በተሞላው ሠዓት በራሱ እንዲጀመር ተደርጎ ትእዛዝ ተሠጥቶት የነበረው ቴሌቪዥን 4፡15pm ላይ ‹ሙሽራዬ ሙሽራዬ የወይን አበባዬ› እያለ ኬክ ስንቆርስ የተሳነውን ቪዲዮ መጫወት ጀመረ፡፡ይህን ጊዜ‹እንዴ ምንድነው የማየው ጉድ፤የት ነው ያመጣኸኝ፤ብላ ደስታ ባለው መገረም በእጇ ይዛው የነበረ አፏን ለቀቀችና የመገረም ሣቋን ታስነካው ጀመር፡፡ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት