Tuesday, February 16, 2010

‹ከዚህ የመጨረሻ ዕድል በኋላ ግን እጃችንን አጣምረን አንቀመጥም ! መረጃዎቻችንን ይዘን የ I.R.S ን በር እናኳኳለን ! ሕዝቡ ግን ያን ጊዜ ይህ ለምን ሆነ እንዳይለን !

ሰላም ተዋሕዶ በአስተዳደር ቦርድ ጤናማ ያልሆነ አሠራር ችግር ምክንያት የተናጋውን የቤተክርስቲያኗን ሰላም አስመልክቶ የችግሩን ምንጮችና ለዚህ አስተዋጽዖ ያበረከቱትን ግለሰቦች በግልጽ ከመተቸት ጀምሮ ምእመናኑ እንዲገነዘቡትና በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ምን እየተደረገ እንደሆን ከውስጥ የምታገኘውን መረጃ መሠረት በማድረግ ስታሳውቅ መቆየቷ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ በመሄዱና ሕዝበ ክርስቲያኑ ለእግዚአብሔር ቤት የሚሠጠውም ገንዘብ ያለይሉኝታ እየተዘረፈና ምሥጢሩም አደባባይ እየወጣ በመውጣቱ ድርጊቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተቆርቋሪዎች ነን የሚሉትን ሁሉ አበሳጭቷል ፡፡ አስቆጭቷል፡፡

በዚህ መሠረት የቤተክርስቲያኗ አባላት በሆኑትና በባለጸግነታቸው በሚታወቁ ጥቂት ተቆርቋሪ ግለሰቦች አነሳሽነት ቤተክርስቲያኗን ከዘራፊዎች የማስጣል እንቅስቃሴ እንደተጀረ የሰሞኑ ዜና ሆኖ ስንብቷል፡፡

እንቅስቃሴው ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የብዙኃኑን ሕዝበ ክርስቲያን ሙሉ ትብብርና ድጋፍ የሚጠይቅ መሆኑም ይታመንበታል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በእንዲህ አይነቱ ስብሰባው ላይ ብንገኝ እነገሌስ ምን ይሉናል ፤ ማኅበራዊ ሕይወቴን ያጨናግፍብኛል የማይባልበትና ለሆድ የሚታሰብበት ጊዜ ባለመሆኑ ለዚህ የመጨረሻና ወሳኝ ተግባር ማንም የቤተክርስቲያኒቱ ወዳጅ የሆነና የዘራፊዎቹን ሤራ የሚቃወም ክርስቲያን ሁሉ በዚህ የስብሰባ አጀንዳ ላይ ተገኝቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማዳን ግዴታውን እንዲወጣ ይህ ጥሪ ለቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አባላትና ለምእመናን ሁሉ ይድረስልን ሲሉ በመረጃ ዙሪያ ለሰላም ተዋሕዶ በጣም ቅርበት ያለቸው ሁለት ሁነኛ ሰዎች ገለጹ ፡፡

ሰላም ተዋሕዶ ከላይ በርእሱ የተቀመጠውን አስደንጋጭ አነጋገር በንዴትና በቁጭት የተናገሩትን የእነዚህ ሁለት ሰዎችን ሙሉ ቃልና አቋማቸውን እንደሚከተለው ዘግቧል፡፡

‹ የቤተክርስቲያኒቱን አጠቃላይ ሂደት እስካሁን በትእግስት ተመልከተናል፡፡ በሽምግልናም ሆነ በክስ የተሞከሩትን ሙከራዎች ሁሉ ውጤቸውን አይተናል፡፡ ዝም ብሎ የተቀመጠውንና ዝምታው ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ የሚደርገውን ሕዝብ የመጨረሻ መልስ እንይ ብለን እንጂ ፤ ሽማግሌም ሆነ ፍርድ ቤተ ያልፈታውን ችግር I.R.S በአጭር ጊዜ መፍትሔ ይሠጠዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህ ደግሞ በእጃችን ያለው በቂ መረጃ እንጂ የሕዝብ ብዛትና ድጋፍ አያስፈልገንም ፡፡ 

ስለዚህ ሕዝብ የእግዚአቤርን ቤት ከዘራፊዎችና ከዓይን አውጣ ቀማኞች መጠበቅ የማይፈልግና ዝም ብሎ የሚመለከት ከሆነ መንግሥት ቤቱን እንዲረከብና በውስጡ ያለውን አሠራር ፈትሾ የራሱንም ድርሻ እንዲተሳሰብና የቤተክርስቲያኒቱንም የወደፊት ሕልውና እንዲወስን ለማድረግ ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆናቸውንና ይህንንም ለማድረግ የመኪናን ሞተር በቁልፍ የማስነሳት ያህል ቀላል እንደሆነ ሕዝቡ ሊያውቀው ይገባል፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱን ለማዳንና የዘራፊዎቹን ጉዳይ ለመወሰን በሁለት ሳምንት ውስጥ ይጠራል የተባለው የተቆርቋሪ አባላት ስብሰባ የመጨረሻ እድል ይሆናል፡፡ 

ከዚህ የመጨረሻ ዕድል በኋላ ግን እጃችንን አጣምረን አንቀመጥም ! መረጃዎቻችንን ይዘን የ I.R.S ን በር እናኳኳለን! ሕዝቡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ እንዳያዝንብን ግን ካአሁኑ አጥብቀን እናስጠነቅቃለን ! › 

 ሕዝቡ አሁንም ቸልተኛ ሆኖ የድርሻውን ለመወጣት ዳተኛ ከሆነ ግን እኛም በስብሰባ ላይ ለመጣው ሕዝብ ይህንኑ አቋማችንን አሳውቀን ይህንኑ ለማስፈጸም በጽናት እንቆማለን ፡፡ ከዚህ በኋላ ቤክርስቲያኒቱ ጥቃቷን የሚያይላት ሕዝብ የሌላት ናትና የመንግሥት ትሆናለች፡፡ ያን ጊዜ ለቅሶ ይሆናል ግን የማይጠቅም ለቅሶ ነው፡፡ ያን ጊዜ ቁጭትና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል ፡፡ ነገር ግን ሁሉም አይጠቅም፡፡›ማቴ 24 ›

ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ መሆኑዋ ቀርቶ የመንግሥት ንብረት ወደ መሆን ከመጣች አስፈላጊ አለመሆኑዋ ታምኖበታል ማለት ነው ? ይህ ከዚህ አስደንጋጭ ዘገባ በኋላ በሰላም ተዋሕዶ ኅሊና ያደረ ጥያቄ ነው ፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሔ ማገኘት እንድንችል ፤ ጥያቄውን ሁላችንም እናሰላስለው ፡፡


No comments:

Post a Comment

አስተያየት