Saturday, July 30, 2011

ከእንቅልፍ የምተነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ ! › ሮሜ 13፡11
ቅዱስ ጳውሎስ እርሱ በሥጋ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ፤ አሁን ያለንበትንም ዘመን ጨምሮ፤ ወደፊት የሚነሳውንምና ዓለም እስከምታልፍበት ዘመን ድረስ ያለውን ትውልድ አካቶ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ዘመኑን በመዋጀት ብዙ ድንቅ ነገሮችን ተናግሮአል፡፡ በሥጋው መከራ በመቀበል የሞተልንን አምላክ እንዳንረሣውና በከበረ ደሙ የመሠረታትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያኑንም በንቃት እንድንጠብቅ ለየአብያተ ክርስቲያናቱ ምዕመናን ከላካቸው የማጽናኛ ፤ የማበረታቻ ፤የማሳሰቢያና የማስጠንቀቂያ አሥራ አራት መልእክቶቹ መረዳት ይቻላል፡፡ 



ቅዱስ ጳውሎስ ከፊተኛው ጊዜ በበለጠ በክርስትና ሕይወታችን እንድንጠነክርና እንድንጸና ሮማውያንን በመከረበት ትምሕርቱ እኛንም እንድንበረታ ያስጠነቅናል፡፡ ‹ ከእንቅልፍ የምተነሱበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ ! › ሮሜ 13፡11 በማለት ከመነቃቀፍና ከመተቻቸት ይልቅ ለሃይማኖታችን አንድ ሆነን ለአንዲት የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ጠበቃ እንድንሆንና ዘብ እንድንቆም ይመክረናል፡፡


እንቅልፍ የሥጋ ድካም ማሳለፊያ ዕረፍት ቢሆንም ቤተክርስቲያን ከደረሰባት ችግር አንጻር ግን ሙሉውን ሌሊት በመኝታ የምናሳልፍበት ጊዜው አለመሆኑንም የራሱን ሕይወት ምሳሌ በማድረግ ይነግረናል፡፡ ‹.... በድካምና በጥረት፤ ብዙም ጊዜ እንቅልፍ በማጣት ፤ በረሀብና በጥም፤ ብዙም ጊዜ በመጾም ፤ በብርድና በራቁትነት ነበርኩ፡፡...›› እያለ ለቤተ ክርስቲያን ሲል ያጣውን እንቅፍና ያየውን መከራ ሁሉ ይዘረዝራል፡፡ 2ኛ ቆሮ 11፡27 ፡፡ 


ዛሬ ግን ብዙዎች እንቅልፍ አጥተው የሚደክሙት ለምንድን ነው ? የተሠራውን ለማፍረስ ? ያለውን አንድነት ለመበተን ? ለራስ ክብር ? ለግል ዝና ? ለሹመት ? ለሥልጣን ? ለምድን ነው ? በአሁኑ ጊዜ ተሐድሶ ከድርጅት ወደ ድርጅት፤ ከግለሰብ ወደ ማኅበር ፤ ከሥውርነት ወደ ግልጽነት ፤ ከፍርሃት ወደ ድፍረት ፤ከአንዲት ከተማ ወደ አገር አቀፍ ፤ከማጀት ወደ አደባባይ እያደገ በመጣበት በዚህ ፈታኝ ሰዓት ማኅበረ ቅዱሳን ለምን እንዲህ ሆኖ ተገኘ ?


ማኅበረ ቅዱሳንስ እስከዛሬ ድረስ እንቅልፍ በማጣት የደከመው ለምንድን ነበር ? ለዚህ ሰሞኑን ለምናየው ውዥንብርና ትርምስ ? ለዚህ ከሆን ወንጌል በዚያ ማኅበር ሕይወት ውስጥ ገና ቦታ አላገኘም ማለት ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የልጆቹን ገበና አደባባይ ካወጣ ፤ ልጆቹም የአባቱ የኖኅን ኃፍረት እንደገለጠው እንደ ካም የማኅበሩን ኀፍረት የሚገልጡና የሚያዋርዱ ከሆነ ወንጌል ታጥፋ ተቀምጣለች ማለት ነው ፡፡ፍልሚያ ለመጀመር የቃላት ሾተልና ጎመድ በአባትና በልጅ እጅ ተይዧል ማለት ነው ፡፡ይህ ደግሞ መጨረሻው ጥፋት ነው፡፡ የማኅበሩ ሥራ አመራር ለአባላቱ ልጆቹን በሥርዓት እንደሚያሳድግ አባት ነው፤ አባላቱም ለአመራሩ በሥርዓት እንደሚታሚታዘዙ ልጆች ናቸው ፡፡ ልጅ ሲያጠፋ አባት ይመክራል ፤ይገሥጻል ፡፡ ይህ በመጽሐፍ ያለ ነው፡፡ የአባት ጥፋትና ስሕተት የሚሆነው ግን ልጁን በቁጣና በኃይል አንተ አታውቅም ልጅ ነህ ፡ እንዲህ ሁን ፡ ብሎ ያለአግባብ በግድ ለማሳደግ ከሞከረ ነው፡፡ የኃይል ሥራ ውጤቱ ደግሞ አያምርም፡፡


ስለዚህ ይህ ለቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሁሉ ተሥፋ የሆነ ማኀበር ከተኛበት እንቅፍል ፈጥኖ በመንቃት አንዱ ሌላውን መኮነንና መተቸቱን አቁሞ አለ የተባለውን መሠረታዊ የሃሳብ ልዩ በውይይት አስወግዶና ስህተቶቹን አርሞ እንደገና የሰላምና የምሥራችን ዜና ይዞ ወደ ሜዲያው መምጣት ይኖርበታል፡፡ የቤተክርስቲያን ልጆች የሆን ሁሉ የምንጠብቀውም የምንመኘውም ይህንኑ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ‹እርስበርሳችሁ ተበላልታችሁ እንዳታልቁ ተጠንቀቁ !› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስጠነቀቀው ያሉትን የማኅበሩን ችግሮች በአስቸኳይ ለመፍታት የማኅበሩ አመራርና አባላቱ ሁሉ ከተኙበት ሊነቁ ይገባል ! እንላለን፡፡

No comments:

Post a Comment

አስተያየት