አዲስ የቤተክርስቲያን ሕንጻ በዳላስ ቴክሳስ !
ከተቋቋመ ገና ሁለት ዓመት ያልሞላው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የዳላስ ደብረ ጸሐይ ቅዱስ ተክለ ሃማኖትና አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ለቤተመቅደስ አገልግሎት ሊውል የሚችል ትልቅ ሕንጻ በ 900.000 ዶላር መግዛቱ ተገለጠ ፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የዳላስ ከተማ ምዕመናን በተገኙበት ታላቅ መንፈሳዊ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሕንጻው ለቤተ መቅደስነት ብቁ የሚያደርጉትን መስፈርቶች ለማሟሟላት እንዲችል የ ሪሞዴሊንግ ሥራ እየተሠራለት እንደሆነ ተገልጧል፡፡ ይህ በቅርቡ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ አገልግሎቱን የሚጀምረው ቤተ ክርስቲያን በምድር በርካታ የቢሮና የሕጻናት ማስተማሪያ ክፍሎች፤ የመመገቢያ አዳራሽና መጸዳጃ ቤቶች ያሉት ሲሆን በፎቅ ላይ ደግሞ ሰፊ ቤተ መቅደስና የሰብከተ ወንጌል አዳራሽ ይኖሩታል፡፡
በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተፈጠረው የአስተዳደር መበላሸት ምክንያት በተፈጠረው ችግር በአሁኑ ሰዓት በርካት ምእመናን ወደ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን እየፈለሱ ይገኛሉ፡፡ ወደዚሁ ሰላማዊ ደብር ለመሄድ የዚሁኑ ሕንጻ ሥራ ማለቅ በጉጉት እየጠበቁ ያሉ በርካታ ምእመናንም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ስብከተ ወንጌሉንና የመንፈሳዊውን አገልግሎት በበለጠ ለማጠናከርና አገልግሎቱን ለማስፋት እንዲረዱ የደብሩ ሰበካ ጉባዔ ጽ/ቤት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውም ለቀው የወጡትን ካህን ቀሲስ መስፍን ደምሴን ፈቃደኛነታቸውን ጠይቆ በመደበኛ አገልጋይነት መቅጠሩንም ይፋ አድርጓል፡፡
No comments:
Post a Comment
አስተያየት