በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተፈጠረው አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት የወጡት ሁለቱ ካህናት መልአከ ሣህል አወቀና ተሰማና ቀሲስ መስፍን ደምሴ ሕዝቡን በአዳራሽ በማሰባሰብና ወንጌልን በማስተማር ማቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ መልአከ ሣህል አወቀ በመኖሪያ ወረቀታቸው ችግር ምክንያት ለዘለቄታው ወደ አትላንታ ቢሄዱም ቀሲስ መስፍን ግን ከጉባኤው አስተባባሪዎች ጋር በመሆን ጉባኤው በተጠናከረ መልክ እንዲቀጥል ማድረጋቸውም ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ቀሲስ መስፍን ባለፈው ዓርብ መጋቢት 16 ቀን ጉባኤው ከተቋቋመ ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ የጉባኤው ደካማና ጠንካራ ጎኖች ምንድን ናቸው ? ወደፊት የጉባኤው መጨረሻስ ምን መሆን ይኖርበታል ? በሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ከጉባኤው ወስጥ በተመረጡ ስድስት ሰዎች አማካኝነት አባላቱ ውይይት እንዲያደርጉ በማድረግ ጉባኤው መድረሻው የት እንደሆነ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡
መንበሩ ኢትዮጵያ በሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ በማትመራ ገለልተኛ ቤተክርስቲያን ውስጥ መቆየትና ፖለቲከኞች ነን የሚሉ አምባገነን የቤተክርስቲያን ቦርድ አባላት በየጊዜው በካህናትና ምእመናን ላይ የሚፈጽሙትን ግፍና በደል እያዩ በዚያ መኖር የክህነቱን ሥልጣንና ክርስትናውን ማዋርድ ሆኖ ስላገኙት ሥራቸውን በፈቃዳችው ለቀው መውጣታቸውን ካህኑ በመግለጥ በአሁኑ ሰዓት ግን የደብረ ጸሐይ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን መደበኛ አገልጋይ ካህን በመሆን እንዲያገለግሉ የተቀጠሩ መሆናቸውንም ለጉባዔው ይፋ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም የስብከተ ወንጌሉን የሠርክ ጉባዔ አገልግሎት ጨምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠብቅባቸውን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሁሉ በእዚያው በአዲሱ የቤተክርስቲያን ሕንጻ ውስጥ ለመስጠት እንዳቀዱም ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ አገልጋዮችን የሚያሳትፉ ልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍሎች እንደተዋቀሩላትና ብዙ ምዕመናንም ቁጭ ብለው ከመማር ተግባር በተጨማሪ ወደ ሚፈልጉት የአገልግሎት ክፍሎች ገብተው የማገልገል ሰፊ እድል እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡በተጨማሪም በአዲሱ መዋቅር ያሉቱን አንዳንድ የአገልግሎት ክፍሎችን ምሳሌ አድርገው በፕሮጄክተር አስክሪን በማቅረብ ሕዝቡ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የኔነት ተሰምቶት ሳይሳቀቅ ማገልገል እንደሚችል በእርሳቸው በኩሉ የተመቻቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በኪራይ እንገለገልበት የነበረው አዳራሽ ባለቤቶች የሌላ እምነት ተከታዮች ቢሆኑም እኛ የተከራየነው ቦታቸውን እንጂ እምነታቸውን ስላልሆነ በቆይታችን ወቅት የቤተ ክርስቲያናችንን ጠቃሚ ትምሕርቶች ተምረንበታል፡፡ የትምህርት መስጫ አዳራሹ ተሥፋ ቆርጦ የተበታተነውም ሕዝብ ተሰባስቦ እንዲጸልይና ታዋቂ መምህራንና ዘማርያንንም በመጋበዝ በዓይነታቸውና በይዘታቸው እጅግ ልዩ የሆኑ ሦስት ታላላቅ ጉባዔያትም ተደርገውበታል፡፡ ስለዚህ ጉባዔው እንደ አንድ ቤተሰብ ሆኖ በመቆት እግዚአብሔርን ሲያገለግል እንደቆየ ሁሉ ወደፊትም የሀሳብና የዓላማ መለያየት ሳይኖር ሰላም በምናገኝበት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ማገልገል እንደሚሻል በመምከር ለእለቱ የተመደበው ጊዜ ስላለቀ ጉባኤውን በጸሎት ዘግተዋል፡፡ ወይይቱና ለአዲሱ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ኅሊናን የማዘጋጃ መማማሪያዎች በቀሪዎቹ የዓርብ ጉባዔያትም እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል፡፡
No comments:
Post a Comment
አስተያየት