ሰላዩ ብዕር ! ክፍል ሁለት
ከባለቤቴ ጋር ከተጋባን አምስት ዓመታት አለፉን ፡፡ በሰላምና በጥሩ ፍቅር አሳለፍን የምላቸው ዓመታት ቢኖሩ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ብቻ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በመካከላችን በሚፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ መነጋገሩ ፤ መወያየቱና መግባባቱ ነበረን፡፡ ከሁለት አንዳችን ቅሬታ የተሰማው ሰው ካለ በግልጽ ‹ በዚህ ጉዳይ ቅር ስላለኝ መነጋገር እፈልጋለሁ › ካለ ሁለታችንም ያለምንም ተቃውሞ ለመነጋገር በደስታ እንቀመጣለን፡፡ መግባባት ባለበት ሥርዓት እንነጋገራለን ፤ እንደማመጣለን፡፡ይህ ባህሪያችን በመካከላችን ያለውን መተማመንና ፍቅር ጥሩ ደረጃ ላይ አድርሶት ነበር፡፡
ሦስተኛው ዓመት ላይ ግን እንደ ባቢሎን ሰዎች ቋንቋችን ተደበላለቀ መሰለኝ ባለቤቴ ለእኔ የሚናገረኝ ነገር ሁሉ አልጥምሽ አለኝ፡፡ሰው ምንም ቢዋደድ በእለታዊ ኑሮው 100% ተግባብቶ ይኖራል ማለት ባይቻልም የእኛ አለመግባባት ግን በሚያስገርም ሁኔታ ወርዶ ዜሮ ቁጥር ላይ ደረሰ፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰን ምክንያት ምን እንደሆነ እኔም አላውቀውም፡፡ በእርግጥ ብዙ ጊዜ ሰው እራሱን ጥፋተኛ ስለማያደርግ ነው እንጂ ጥፋቱ ሙሉ ለሙሉ የእኔ ነው ማለት እደፍራለሁ፡፡ የእኔ ጠባይ በባለቤቴ ላይ በጣም እንደተቀየረ ቢታወቀኝም የምሠራውና በቁጣ ስሜት ሆኜ የምናገረውን ክፉ ቃል ሁሉ ለማሻሻል ብጥርም ተምልሼ ግን እዚያው ነኝ ፡፡
ባሳለፍነው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የመነጋገርና የመወያየት ባህላችን ለመቀጠል ባለቤቴ ብዙ ቢጥርም እኔ ግን ፈላጎቱ ከልቤ ስለጠፋ ጊዜን እንደማጥፋትና እንደኋላ ቀርነት እቆጥረው ጀመር፡፡ የተሠራውን ምግብ አብረን ተቀምጠን እንበላለን እንጂ እንደድሮው መጎራረስ ግን አቁመናል፡፡ ባለቤቴ ሊያጎርሰኝ ቢሞክርም አጸፋው የማየቅደረድር እምቢታና ቁጣ ስለሚሆንበት ሰላም ለማግኘት ሲል ሳይወድ በግዱ ትቶታል፡፡በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን አሁን አሁን በጣም የሚገርመኝና የሚደንቀኝ የባለቤቴ ገደብ የሌለው ትዕግስቱ ነው፡፡ እኔ ባመነጫጭቀውም ባለቤቴ ከሥራ በመጣሁ ቁጥር የሚያደርግልኝ የፍቅርና ጨዋነት የተሞላው አቀባበል ግን ፈጽሞ አልተቀየረም፡፡ ከሥራው ወጥቶና ከእኔ ቀድሞ እቤት የመገኝት እድል ስለነበረው ምግብ ሠርቶ፤ ገበታ ዘርግቶ፤ ቤቱን አስተካክሎ ፤ እርሱም ሻወር ወስዶ ገና ከሥራ እንደመጣ ሰው ሆኖ ክራባቱን አስሮ ሱፉን ግጥም አድርጎ ፤ አንዳንዴም በክራባትና በሸሚዝ ሆኖ ይጠብቀኛል፡፡ ስገባም ከልብ በሆነ ፈገግታ ይቀበለኛል፡፡ድሮ ድሮ በጣም ደስ ይለኝ ነበር በኋላ ግን ሰለሰቸኝና ይህ ሁሉ ደንታ አልሰጥሽ አለኝለኝ፡፡እኔ እንደዛ እያመነጫጨኩት እርሱ አንዳች ሳያጠፋ መልሶ ስላስቆጣሁሽ ይቅርታ አድርጊልኝ ብሎ እጁን ትከሻዬ ላይ ጣል ሲያደርግ እኔም በንዴት እጁን አንስቼ ውርውር አደርገዋለሁ፡፡ ምን እንደዚያ እንደሚያደርገኝ ግን አላውቀውም፡፡ ካደረኩት በኋላ ግን ከፊቱ ዘወር ብዬ እጸጸታለሁ፡፡ ትንሽ ቆይቼ እመለስና ይቅርታ ቅድም ስላመናጨኩህ እለዋለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ ባለቤቴ የሚሰማውን ደስታ ልናገረው ባልችልም ብዙም ሳቆይ ደግሞ በአንድ ነገር ተናድጄ ስጮህ ደግሞ ሽምቅቅ ይላል፡፡ ብቻ የኔን ነገር መተው ብቻ ነው፡፡
ለልደቴ ቀን የወርቅ ስጦታ ፤ለፍቅረኛሞች ቀን ቀይ ጽጌ ረዳ ፤ ለፈረንጆች ገና በዓል የውድ ልብሶች ስጦታ፤ለዓመታዊ የጋብቻ በዓላችን እራት ማውጣት ወዘተ... በፍቅር የሚያደርጋቸው መልካም ተግባራቱ ሁሉ የጥሩ ሰውነቱ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ አድራጎቱን ሁሉ ለጊዜው በደስታ ብቀበላቸውም ደስታዬ ከሦስትና ከአራት ሰዓታት በላይ የሚቆዩ አይሆኑም፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ፡፡ እንደተለመደውና ባለቤቴ በየአመቱ እንደሚያደርገው 5ኛው የጋብቻችን ዓመት አንድ ሣምንት እንደቀረውና በልዩ ሁኔታ ልናከብረው እንደሚገባን፤ እርሱም ለዚህ ከወትሮ በተለየ መልኩ እንደተዘጋጀ ነገረኝ፡፡ አልተቃወምኩትም፡፡ በቀጣዩ ቀን ፕሮግራሙ በባለቤቴ እየተመራ ዝነኛው ባለ ብዙ ኮከብ በሆነው Rennasiance Hotel 4፡00 ላይ ደረስን፡፡ ይቀጥላል፡፡
No comments:
Post a Comment
አስተያየት