ረዳት ካሜራ
ክፍል ሦስት
እኔም በበኩሌ የባለቤቴ ጠባይ ባልተጠበቀ ሁኔታ መለወጥና በትዳራችን መካከል የነበረው ጣዕም ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ መምጣት እጅግ በጣም አሳስቦኝ ነበር ፡፡ እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ ከእርሷ ጋር ለመኖር ወስኜና ወድጃት ያገባኋት የትዳር ጓደኛዬን ከምንም በላይ እወዳታለሁ፡፡እርሷ ስሜታዊ ሆና በየምክንያቱ ብትበሳጭም ብስጭቷን የሚያበርድ እንጂ ንዴቷን የሚጨምር ሥራ ሠራሁ የምለው በእኔ በኩል አንዳች ነገር የለም፡፡እሷን የሚያስቀይም መጭፎ ነገር ማደረጌም ጨርሶ ትዝ አይለኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለምታሳየኝ አክብሮት ለሌለው ሥነ ምግባሯ ቂም ይዤ ወይም እርሷን በክፉ ለመበቀል በጭራሽ አልሜም አስቤ አላውቅም፡፡የእኔ የሁሉ ጊዜ ምኞት እርሷ በአእምሮዋ ታድሳና ተለውጣ ማየት ነው፡፡ ወዲያው መልሳ ብትረሳውም ከእርሷ ያየሁትና የምወድላት መልካም ነገር ቢኖር ካጠፋች በኋላ የምታደርገው ጸጸት ነው፡፡ ያ እንዳልሰለቻትና እንዳልጠላት አድርጎኛል፡፡