እንዳትለያዩ እለምናችኋለሁ !
‹ወንድሞቻችን ሆይ !ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ እንዳትለያዩ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆናችሁ አንድ ቃል ትናገሩ ዘንድ በአንድ ሃሳብም ትመሩ ዘንድ በጌታችን ፤ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥም እለምናችኋለሁ፡፡›1ኛ ቆሮ 1፡10
ቅዱስ ጳውሎስ በ 50 ዓ.ም ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ገብቶ ወንጌልን አስተምሮ የቆሮንቶስን ሰዎች ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ፤ ከኃጢኣት ኑሮ ወደ ቅድስና ሕይወት መለሳቸው፡፡ ጌታም ለሐዋርያነት ሲጠራው ‹በአሕዛብ ፊት ስሜን ትሸከም ዘንድ ምርጥ ሐዋርያ አድርጌ ሾሜሃለሁ፡፡ ›ሐዋ 9፡15 ብሎ እንደ መሠከረለት ብዙ አሕዛብን በወንጌል አስተምሮ ወደ ክርስትናው በረት አስገብቷል፡፡
ይሁን እንጂ በኤፌሶን ከተማ ወንጌልን በማስተማር አገልግሎት ላይ ሳለ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እርሱ ያስተማራቸውን የወንጌል ትምህርት ረስተው እርስ በእርሳቸው ተለያይተው እኔ የአጵሎስ ነኝ ፤ እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ ደግሞ የእገሌ ነኝ በማለት ተከፋፍለው እየተከራከሩ የዋሆች ክርስቲያኖችን እያስበረገጉ መሆናቸውን ሲሰማ እጅግ በጣም አዘነ፡፡ ምክንያቱም ከመለያየትና ከመከፋፈል መፍረስና መበታተን እንጂ ሌላ ዋጋ የለውምና ፡፡ ማቴ 12፤25፡፡
የእግዚአብሔር ሰው መሪው መንፈስ ቅዱስ ፤ ዓላማው መስቀል፤መንገዱም ሕገ እግዚአብሔር ነው፡፡ከዚህ በተለየ ዓላማ በእልከኝነትና በአድማ መጓዝ ክርስትናን የሚያስክድ ከእግዚአብሔር አንድነት የሚለይ ሕይወተ ሥጋንና ሕይወተ ነፍስን የሚያጠፋ ክፉ መንገድ ነው፡፡ ማቴ 12፡30
ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸው እንዳትፍርስና እነሱም እንዳይበታተኑ ከላይ ያየነውን መልዕክት ጽፎላቸዋል፡፡ ከሚደርስባቸው ፈተናዎች ሁሉ መታደግ እንዲችሉም አንድ ሁኑ በማለት በሚገባ መክሮአቸዋል፡፡ ይህ ምክር ፍቅርና አንድነትን ላጣነው ለእኛ በዚህ ዘመን ለምንኖር ክርስቲያኖች እጅግ የሚሠራ ጠቃሚ ምክር ነውና ሁላችንም እንጠቀምበት !
ይህንን ጠቃሚና አጭር የሕይወት ቃል በአስተያየት መስጫ ሳጥን ውስጥ ላስቀመጡልን ለመ/ር ዘወንጌል እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡
No comments:
Post a Comment
አስተያየት