የጁን 26 ሕዝባዊ ስብሰባ በመልካም ሁኔታ ተጠናቀቀ !
በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርቲያን አስተዳደር ችግር ምክንያት የተናጋውን የቤተክርስቲያኒቱን ሰላም በውይይት ማስተካከል ባለመቻሉ ጉዳዩ እጅግ ባሳሰባቸው በርካታ ምእመናን በሜይ 8ቱ ሕዝባዊ ስብሰባ ተወክሎ ጥረቶችን ሲያደርግ የሰነበተው የመፍትሔ ፈላጊ ኮሚቴ ቅዳሜ ጁን 26 ቀን 2010 በተጠራው ሁለተኛ ዙር ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ስላከናወናቸው ተግባራት ሪፖርቱን አቀረበ፡፡ በሜይ 8ቱ የምእመናን ስብሰባ ውክልና የተሰጠው የመፍትሔ ኮሚቴ ከቦርዱ ጋር በግንባር ተገናኝቶ ለመወያየትና የሕዝቡን ጥያቄ ለማቅረብ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለትና ቦርዱ ጨርሶውኑ አላውቃችሁም በማለት ሊያናግራቸውም ሆነ የሕዝቡንም ጥያቄ ሊቀበል እንዳልፈለገ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡
ይሁን እንጂ ባሉት የሰላም መንገዶች ሁሉ የሰላሙ ሙከራ እንዲደረግና ጥረቶቹ ሁሉ ጽሑፋዊ መረጃ እንዲኖራቸው ታስቦ እንጂ የአስተዳደር ቦርዱ ሰላም ፈላጊ አካል አለመሆኑ ቀደም ሲልም ተረጋግጧል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ሕዝቡ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን የውሳኔ ሃሳቦች በሙሉ ድምጽ አሳልፏል፡፡
1. የቤተክርስቲያናችን ዋና ችግር የአስተዳደር ቦርድ መሆኑ በይፋ የታወቀውና በብዙኃኑ ሕዝበ ክርስቲያን አእምሮ ውስጥ ስርጾ የገባው አሁን በመሆኑ የቦርዱ አጥፊነት ቀድሞ የገባቸው ጥቂት የቤተክርስቲያኑ አባላት ግን የቦርድን ጥፋት በሕግ ለማስቆም በፍርድ ቤት መክሰሳቸው አግባብነት ያለው መሆኑን ሕዝቡ በሙሉ ድምጽ በማረጋገጥ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በቅርብ የተጀመረው ክስ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥልና ሙሉ የዚህ ሕዝብ ድጋፍ እንዲሠጠው ፡፡
2. የመፍትሔ ኮሚቴው ሥራውን አመርቂ በሆነና ሙያዊ በሆነ መንገድ በትክክል እየሠራ ያለና ወደፊትም ለማኅበረሰባችን መሪነቱ በአርዓያነት የሚጠቀስ አካል በመሆኑ ባለበት የመሪነት ቦታ እንዲቀጥልና የሕጉን እንዲሁም የክሱን ሂደት ቀደም ብለው ከጀመሩት የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ጋር በመሆን በአንድነት እንዲሠራ ፡፡
3. ለጊዜው ያለው መፍትሔ ጉዳዩን በሕግ መከታትልና የአስተዳደር ቦርዱን አሉታዊ አሠራር በዚሁ መንገድ ማስቆም ስለሆነ የመፍትሔ ኮሚቴው ለዚህ ጉዳይ የሚያስፈልጉ ረዳት ኮሚቴዎችን በሥሩ አዋቅሮ እንዲሠራ፡፡ በማለት የእለቱ ስብሰባ አጀንዳ ፍጻሜ ሆኖአል፡፡
በመቀጠልም ‹አገልግሎታችንና እንቅፋቶቹ › በሚል ርእስ ቀሲስ መስፍን ወቅታዊና ቀሽቃሽ የወንጌል ትምሕርት የሰጡ ሲሆን በማስከተልም መልአከ ሣህል አወቀም አጠናካሪ ምክርና ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበው በማጠቃለያ ጸሎት የስብሰባው ፍጻሜ ሆኗል፡፡
No comments:
Post a Comment
አስተያየት