ጌታችን እና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድህነተ ዓለምን ከፈጸመ በኋላ መስቀሉ ሕሙማነ ስጋን በተአምራቱ የሚፈውስ፣ የዳሰሱትን ሁሉ የሚያድን ሆኗል። በዚህ ተዓምራት የተሳቡ አንድ አንድ አይሁዶችም ክርስቲያኖች ይሆኑ ነበር። ይህ ያስቆጣቸው አይሁዶች ደግሞ መሬት ቆፍረው ቆሻሻ ደፍተው እና ተራራ ሰርተው መስቀሉን ቀበሩት። በዚህ ሁኔታ ለሶስት መቶ አመታት መስቀለ ክርስቶስ ተዳፍኖ ቆየ።
በሮም ላይ ነግሰው ከነበሩት ደጋግ ነገስታት ቆስጠንጢኖስ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነገሰ። ንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናቱ እሌኒ በልዩ ክርስቲያናዊ ህይወት ኮትኩታ ያሳደገችው ክርስቲያን ንጉስ በመሆኑ በዘመነ መንግስቱ የክርስቲያኖችን ነጻነት ያወጀ ነበር። እናቱ ቅድስት እሌኒ በአረጋዊ ኪራኮስ ምክር ደመራ አስደምራ፣ እጣን አስጢሳ ሊቀ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ዘእጣን አንጾረ ሰገደ ጢስ” እንዲል፤ የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች በመመለስ መስቀሉ ያለበትን ስፍራ አመለከታት። ለዘመናት ተቀብሮ የኖረውን መስቀል አስቆፍራ አወጣችው።
ለድህነተ አለም ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋውን የቆረሰበት ደሙን ያፈሰሰበት እጸ መስቀል በአረማዊያን ዘመን ቢቀበርም ክርስቲያኖች ነጻነት ባገኙበት የሰላም ዘመን ወጣ። ሲወጣም እወር በማብራት፣ አንካሳ በማርታት፣ ጎባጣ በማቅናት፣ ለምጽ በማንጻት፣ ሙት በማስነሳት ተዓምራት አድርጓል።
ሰለ ክብረ መስቀል ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ቅዱሳት መጻህፍት እና የልዩ ልዩ ጉባኤያተ ቀኖናት ያወሳሉ። ነገረ መስቀል የማናቸውም አገልግሎት መግቢያ በር እንደመሆኑ መጠን ካህናት በእጀ መስቀላቸው፣ ምእመናን በትምህርተ መስቀል ማማተብ ከተግባሮቻችን ሁሉ ቀዳሚ ነው።የመስቀሉ በረከት በሁላችንም ይደር አሜን !