Wednesday, June 22, 2011

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አለን? ዓላማውና ስልቱስ ምንድን ነው?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “መታደስ አለባት” የሚሉ ድምፆችን የሚያሰሙ አካላት አሳባቸውን በተለያዩ መንገዶች ማሰማት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ እነዚህ አካላት በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች፣ በመጻሕፍት፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ በዓውደ ምሕረት ስብከቶችና በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ይኸን ጩኸታቸውን ማስተጋባቱን ተያይዘውታል፡፡ እንዲህ እያሉ ያሉትም “ኦርቶዶክሳውያን ነን” እያሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተለያየ ቦታና ሓላፊነት ላይ ካሉና እንጀራዋን ከሚበሉ፣ ጥቂቶች እንዲሁም ደግሞ በኅቡእና በግልጽ በተለያየ መልክና ቅርጽ ራሳቸውን አደራጅተው ቤተ ክርስቲያኗ ሳትወክላቸው እርሷን ወክለው፣ “እኛም ኦርቶዶክስ ነን” በሚል ካባ ራሳቸውን ደብቀው እምነቷንና ሥርዓቷን “ይህ ሳይሆን ሌላ ነበር” እያሉ ፕሮቴስታንታዊ ትምህርትና መንፈስ የተዋረሳቸው ሰዎች ናቸው፡፡

ተሐድሶ የሚባል ነገር አለን? እነዚህ አካላት በአንድ በኩል ተሐድሶ የሚባል ነገር እንደሌለና ተሐድሶ የሚባለው ጉዳይ የሆነ አካል (እነርሱ እንደሚሉት ማኅበረ ቅዱሳን) ስም ለማጥፋት ሲል የፈጠረው የፈጠራ ወሬ እንጂ በሕይወት የሌለ ምናባዊ ነገር እንደሆነ ያስወራሉ፣ ይናገራሉ፡፡ ግን በእውነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ መታደስ አለበት በማለት የሚሠራ የተሐድሶ እቅስቃሴ የለምን?


ይህን ጉዳይ እነርሱው በይፋ ካወጧቸው የኅትመት ውጤቶቻቸው ለመመልከትና ለመታዘብ ይረዳ ዘንድ ራሳቸው በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸው፣ መጽሔቶቻቸውና ጋዜጦቻቸው ካወጧቸው መካከል የተወሰኑትን ብቻ እንመልከት፡-
“እንደ እውነቱ ከሆነ በወንጌል እውነት ከታደሱ በኋላ በየጊዜው እየተመዘዙ የወጡት ምእመናኖቿና አገልጋዮቿ በውስጧ ቆይተው የተሐድሶን ሥራ እንዲሠሩ ቢደረግ ኖሮ፣ በወንጌል ተሐድሶ ያገኙ ክርስቲያኖች ለዓመታት የጸለዩበትንና የጓጉለትን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ በቅርብ ጊዜ ሊያዩ ይችሉ እንደ ነበር የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት 2002፣ ገጽ 15)

“ተሐድሶ እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ እንቅስቃሴም ውጤታማና ትርፋማ ይሆን ዘንድ ዓላማን፣ ሒደትንና ግብን የያዘ ድርጊት እየተከናወነበት ያለ ሊሆን ስለሚገባው፣ ያለፈውና እየሆነ ያለው ግብረ ተሐድሶ ተመዝግቦ ለአሁኑና ለሚመጣው ትውልድ በሥነ ጽሑፍ ዳብሮና አምሮ ሊቀርብለት ይገባዋል፡፡” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት2002፣ ገጽ 17) “በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተን አረሞችን በገሀድ ካልነቀልን ተሐድሶን እንዴት ልናመጣ እንችላለን? መባሉ አይቀርም፡፡ ዳሩ ግን ስሕተቶችን ፊትለፊት ሳይቃወሙ ስሕተቶች እንዲታረሙ ማድረግ የሚቻልባቸው የተፈተኑ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌም …” (ኆኅተ ብርሃን፣መጋቢት 2002፣ ገጽ 19)

“ከ2000 ዘመናት በላይ ያስቆጠረች የእኛ ቤተ ክርስቲያንማ እንዴት አብልጦ ተሐድሶ (መታደስ) አያስፈልጋት?” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 15) “ቤተ ክርስቲያናችን በክፉ ሰዎች ሴራ ዓላማዋን ስታለች፣ የሐዋርያትንም ትምህርት ገፍታለች፣ ስለ ሆነም ይህን የሐዋርያት ትምህርት በክፉዎች ምክንያት በመጣሱ በድፍረት ተሳስተሻልና ታረሚ ልንላት፣ በድፍረትም በሥልጣንም ሕዝቡን ልናስተምር ይገባል፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 20) “ቤተ ክርስቲያናችን በየሀገሩ የተነሣውን የተሐድሶ የወንጌል እሳት በተለይ በሐረር፣ በባሕር ዳር፣ በአዲስ አበባ፣ በማርቆስ፣ በጎንደር፣ በሰሜን ሸዋ፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በባሌ ለማዳፈን ያን ሁሉ እልፍ አእላፍ ሠራዊት የቤተ ክርስቲያን አለኝታ ወጣት ወንጌል ባልገባቸው ምእመናንና ካህናት እያስደበደበች ለሌላ ድርጅት አሳልፋ ከመስጠት ይልቅ ስሕተቷን አርማ ልጆቿን በጉያዋ ብትይዝ ኖሮ ዛሬም ጭምር ጋብ ላላለው ፍጥጫ አትዳረግም ነበር፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 16) “ሕዝባችን በልማድና በባህል ሃይማኖትን መያዙና ይህን የያዘውን ሃይማኖት ለመጣልና ለማጣራትም በቂ እውቀት ስለሚጎድለው በራሱ አንብቦ መረዳት ስለማይችል …” (የሚያሳውቁት ሃይማኖትን ለማስጣል ነው ማለት ነው) (ይነጋል፣ 1997፣ ገጽ 144)

እነዚህ እነርሱው ከጻፏቸውና አሳትመው ካሰራጯቸው መካከል ለአብነት ያህል የተጠቀሱት በግልጽ የሚያሳዩን ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ትምህርት የሚቃወሙና ሊለወጥ ይገባል የሚሉ ራሳቸውን “ተሐድሶ” የሚል ስያሜ ሰጥተው በተለየ መልክና ቅርጽ በግልጽና በኅቡእ እየሠሩ ያሉ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡ ራሳቸው እንዲህ በይፋ “እኛ አለን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ ቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል” እያሉ እየተናገሩ “አይ፣ ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም” ማለት እንዴት ይቻላል?

ዓላማቸው ምንድን ነው? ተሐድሶዎች ዋና ዓላማቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖናና ትውፊት በመለወጥ ፕሮቴስታንታዊ ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ምእራባውያን ሚሲዮናውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አጥፍቶ ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ መሥራት ከጀመሩበት ከሃያኛው መቶ ዓመት መጀመሪያ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ሦስት ስልቶችን ተጠቅመዋል፡፡ የመጀመሪያው እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ የሠሩበት ስልት ሲሆን እርሱም የራሳቸውን አስተምህሮ ማስተማር ነበር፡፡

ከ1950 ዓመት ጀምሮ እስከ 1990 ዓ.ም ድረስ ደግሞ የሠሩት የራሳቸውን እምነት መሰበክ ሳይሆን በዋናነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመንቀፍና በማጥላላት ምእመኑ እንዲኮበልል በማድረግ ነበር፡፡


ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን እየሠሩበት ያለው ሦስተኛው ስልት ደግሞ "ኦርቶዶክስ ነኝ" ብሎ ውስጧ ገብቶ “ትታደስ” እያሉ በመጮኽ ቤተ ክርስቲያኗ እንዳለች እንድትለወጥ በማድረግ ምእመናኗን ከእነ ሕንፃዋና አስተዳደራዊ መዋቅሯ መረከብ ነው፡፡ የእነርሱ ምኞትና እቅድ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ወደ ሦስተኛው ሺሕ እንዳትሻገር ማድረግ ነበር፡፡ ነገር ግን እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ በዚህም ብስጭታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም ፓውልባሊስኪ (Paul Balisky) የተባለ “የዓለም አቀፍ ተልእኮ ማኅበር” የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በ1992 ዓ.ም በወጣው “የክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር” በተባለ መጽሔት በሰጠው ቃለ መጠይቅ የደከሙት ድካምና ያወጡት ገንዘብ ሁሉ ወደ ጠበቁት ግብ እንዳላደረሳቸው፡-

“ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም ወንጌላውያኑ አሁን በማደግ ላይና በመካከለኛ ኑሮ ላይ ያለውን የከተማውን ኅብረተሰብ መቀየር አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም የተማረና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከፍተኛ ቅንዓት ያለው የወጣቶች ኃይል ማኅበረ ቅዱሳን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሃያ አንደኛው መ/ክ/ዘመን ዘልቃ መጓዝ ትችል ዘንድ እየተጋደለ ነውና፡፡” በማለት ከሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በፊት የማጥፋት ሕልም እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡(The Christian Science Monitor, 8 June, 2000)

ስለሆነም ከዚያ በፊት ያደርጉት እንደነበረው በውጭ ሆኖ ምእመናንን ለመንጠቅ በመሥራት ብቻ ካሰቡት ቤተ ክርስቲያኒቱን ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ግብ ለመድረስ ቀላል እንዳልሆነ ተረዱ፡፡ ስለዚህ አዲስ ስልት መቀየስ አስፈለጋቸው፡፡ ይህም “እናድሳለን”

በሚል ሽፋን ከውጭ ወደ ውስጥ ሠርጎ በመግባት ምእመኑን እስከ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ የመረከብ ስልት ነው፡፡ ይህንም ኬንያ ውስጥ የሚታተመው “The Horn of Africa, Challe nge and opportunity” የተባለው መጽሔት “ዓላማው አዲስ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት አይደለም፤ ቤተ ክርስቲያኗን (ኦርቶዶክስን) መለወጥ (ፕሮቴስታንት ማድረግ) እንጂ - The objective is not to set up a new church as such but to introduce reforms within the church” በማለት ገልጾ ነበር፡፡ (The Horn of Africa, Challenge and opportunity, p. 6)

ስለዚህ አዲሱ ስልት “የጥንቷ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ነበረች - The ancient orthodox was the right Church” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያንን ከውጭ ከመቃወም ይልቅ ውስጥ ገብቶ ምእመን፣ ካህን፣ መነኩሴ፣ ሰባኪ … መስሎ ከፕሮቴ ስታንት እምነትና ባህል ውጭ ያለውን ነገር ሁሉ “ይህ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት አይደለም፣ ይህን እገሌ የጨመረው ወይም የቀነሰው ነው … ’ እያሉ ቤተ ክርስቲያኗ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ በሙሉ ጠፍቶ ሙሉ በሙሉ ፕሮቴስታንት እስክትሆን ድረስ መሥራት ነው፡፡

ይህን ስልታቸውንም በኅትመቶቻቸው በይፋ ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌም በአንድ ስልታቸውን ይፋ ባደረጉበት መጽሔታቸው ላይ እንዲህ ብለዋል፡-

“ታዲያ እርሷን (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን) የማዳኑ ሥራ ከየት ይጀምር? እዳር ሆኖ አንዳንድ ምርኮኛን ማፍለሱ የሚፈለገውን የኦተቤን ተሐድሶ ሊያመጣ ይችላልን? አገልግሎቱ ከየት ወደ የት ቢሄድ ይሻላል? ማለት ከውስጥ ወደ ውጭ ወይስ ከውጭ ወደ ውስጥ? በውስጧ እያሉ የወንጌል እውነት ለተገለጠላቸው አገልጋዮቿ እንደ ውጊያ ቀጠና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ምሽግ በአሁኑ ጊዜ የማስለቀቅና የጠላትን ወረዳ ከጥቃት ነጻ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ያለው በሁለት ወገን ነው፤ … ” ይልና ቀጥሎም ወደ ግባቸው ለመድረስ መደረግ አለበት ያሉትን እንዲህ ዘርዝረዋል፡-


ውስጥ ያሉት እግዚአብሔር በሰጣቸው የውጊያ ቀጣና ውስጥ ሆነው በታማኝነት በእግዚአብሔር ቃል ምስክርነትና በጸሎት ውጊያውን መቀጠል አለባቸው፡፡ በውስጥ ላለው ለዚሁ ውጊያ በወንጌል የታደሱ ክርስቲያኖች ሁሉ እንደ ሙሴ እጃቸውን ወደ ላይ በማንሣት ታላቁን ርዳታ ማድረግና በደጀንነት መቆም ይገባቸዋል፡፡

እነዚህ በወንጌል ተሐደሶ አግኝተናል የሚሉ ሁሉ በውጭ ሆነው ወደ ውስጥ የሚያደ ርጉትን ውጊያ መቀጠላቸው እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለውስጠኛው ውጊያ የሚያገለግል ትጥቅ ያላቸውን ወደ ውስጥ ማስገባትና የውስጠኛውን የውጊያ መስመር ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡

“ … በዚህ የተቀናጀ ስልት መንፈሳዊው ጦርነት ቢቀጥል በውስጥ የተሰለፈው ሠራዊት (በተሐድሶ ስም የሚሠራው የፕሮቴስታንት ክንፍ) እያጠቃ ወደ ውጪ ሲገሰግስ፣በውጭ ያለውም (በግልጽ ፕሮቴስታንት ሆኖ የሚሠራው) ከበባውን አጠናክሮ ወደ ውስጥ ሲገፋ እግዚአብሔር በወሰነው ቀን የውስጡና የውጪው ሠራዊት ሲገናኙ በውስጧ የመሸገው ጠላት መሸነፉን በሚመለከት በአንድነት የድል ዝማሬ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት 2002 ዓ.ም)


ይህ ሁሉ የሚያሳየው

ሀ) በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ በይፋ የተቀናጀ ጦርነት ያወጁባት መሆኑን፣

ለ) የጦርነቱ አንዱ ስልት ውስጥ ሆኖ በውስጥ አርበኝነት መሥራትና መዋጋት መሆኑን፣

ሐ) የጦርነቱ ዓላማ ጠላት የተባለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማፍረስ መሆን ነው፡፡


የተሐድሶው ዘመቻ ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

ተሐድሶዎች ያሰቡትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እንዳለች ፕሮቴስታንታዊ አድርጎ ለውጦ ለመረከብ ያላቸውን ምኞትና ዓላማ እውን ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሀ) የሐሰት ውንጀላዎችን መፍጠርና ማሰራጨት ሌባ ሲሰርቅ የሚያየውን ወይም መስረቁን ያወቀበትን ሰው ይወዳል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ እንደዚሁም እነዚህ በውጫቸው የቤተ ክርስቲያንን ለምድ የለበሱ፣ በውስጣቸው ግን ኦርቶዶክሳዊ የሆነውን እምነትና ባህል አጥፍቶ የምእራባውያን ባህል ተሸካሚ ለማድረግ የሚሠሩ ክፉ ሠራተኞች (ፊል.3÷2) ዓላማቸውንና ስልታቸውን የሚያውቅባቸውን ማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ማኅበር አምርረው ይጠሉታል፣ ይፈሩታልም፡፡፡ በእነ ማርቲን ሉተር በአውሮፓ ተካሒዶ ምእራባውያንን ወደ እምነት አልባነትና ክህደት ማድረሱን ዛሬ በተግባር ያስመሰከረውን ተሐድሶ (ፕሮቴስታንት) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ላይ እውን በማድረግ ይሁዳ ስለ ሠላሳ ብሩ ሲል ጌታውንና አምላኩን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመሸጥ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጋር “አሳልፌ እንድሰጣችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” (ማቴ.!1÷05) ብሎ ጌታውን ለሽያጭ እንዳቀረበ፣ እነዚህም ስንቅና ተስፋ የሚሰጧቸውንና ስልት ነድፈው ከርቀት እያሳዩ የሚያሠሯቸውን የላኪዎቻቸውንና የጌቶቻቸውን ምኞት ለማሳካት እንቅፋት ይሆኑብናል የሚሏቸውን ሁሉ ማሩን አምርረው ወተቱን አጥቁረው በማሳየት ስማቸውን በማጥፋት እንዲጠሉ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ከዚህ ተግባራቸው ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ በተሰጠው ሕገ ደምብ መሠረት በአባቶች ቡራኬና ፈቃድ የተመሠረተውንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆኖ ዓቅሙ በፈቀደ መጠን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውንና ይህን ለቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አደገኛ የሆነ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ምንነት በማጋለጥ ለሕዝብ የሚያስረዳውን ማኅበረ ቅዱሳንን ስሙን በኅትመቶቻቸውና በልዩ ልዩ መንገድ ማጥፋትና ሰይጣናዊ አስመስሎ መሳል አንዱ ስልታቸው ነው፡፡ ለአብነት ያህልም የሚከ ተሉትን እንመልከት፡-


“ማቅ (ማኅበረ ቅዱሳን) ያለ እኔ ቤተ ክርስቲያን፣ ሀገርና መንግሥት የለም ብሎ በጭፍን የሚያስብ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሌላ መንፈሳዊ ማኅበርም ሆነ ጉባኤ ለማየት ዓይኑ የተሸፈነ ነው፡፡ ራሱን የቅዳሴ፣ የቅኔና የመጻሕፍት ማስመስከሪያ ቤተ መምህራን አድርጎ በማየቱ በእርሱ እጅ ፈቃድ ያላገኙ ሰባክያንና መዘምራን ቢፈጠሩ የተለመደው የኮሚኒስቶች ፍልስፍና (የሀሰት ስም የማጥፋት ቅስቀሳውን) ያወርድባቸዋል፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2002፣ ገጽ 1፣ርእሰ አንቀጽ)

እንግዲህ ይህን የሚለው አካል በግልጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሐድሶ ያስፈልጋታል እያለ በዚሁ ጋዜጣ የገለጸው የተሐድሶ ድርጅት ነው፡፡ ልዩነቱ የዓላማ መሆኑን ራሳቸው ተናግረው ሲያበቁ እንደገና መልሰው ተሐድሶ መባልን የሐሰት ስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ይላሉ፡፡ አንባቢዎቻቸው ይህን እንኳን ማገናዘብ አይችሉም ብለው ይሆን?

“የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርት እግዚአብሔር ፍጹም ጨካኝ ስለሆነ ስለማይሰማንና በርኅራሄ ከእርሱ የተሻሉ ቅዱሳን በፊቱ ቆመው እንዲለምኑልን የእነርሱ ልመና ግድ ብሎት ስለሚምረን በአማላጅነት እንመን ይላል፡፡” (ይነጋል፣ 1997 ዓ.ም. ገጽ 123) “ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ይህ የሰይጣን ማኅበር አሁን ወደ ነፍሰ ገዳይነት ሊገባ ራሱን እያዘጋጀ ነው፡፡” (ይነጋል፣ 1997 ዓ.ም.ገጽ 127) ይህ የስም ማጥፋት ዘመቻ በሀገር ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ዋናው የተሐድሶ ዘመቻ አርቃቂዎችና ስልት ነዳፊዎች በሆኑት በምእራባውያን ፓስተሮችም በብዛትና በዓይነት የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም ዊሊያም ብላክ የተባለው አሜሪካዊ ፓስተር አናሲሞስ በተባለው የጦማር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ማፈራረስ እንደሚቻልና በአሁኑ ወቅትም የእርሱና መሰል ድርጅቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እየተዋጓት እንደሆነ “Struggle for the soul of the Ethiopian orthodox Church” በተሰኘው ጽሑፉ ላይ በሰፊው ገልጧል፡፡ የፕሮቴስታንት ጉዳይ አስፈጻሚ የሆነው የተሐድሶ አንቅስቃሴ ምን ማለት መሆኑን ለዓላማቸው መሳካት እንቅፋት ሆኖብናል ያለውን ነገር ሲናገር ገልጾታል፤ እንዲህ ሲል፡-

“Working against both the ongoing creep of Western values and the attempts by Reformists to restore the church, a reactionary movement called Mahebere Kidusan and led by members of the hierarchy and priests and others, are seeking to fend off any changes and to preserve aspects of the Church which they feel are crucial to their identity and Ethiopia’s place in the world. …

በሀገሪቱ ውስጥ እየተንሰራፋና ሥር እየሰደደ ያለውን ምእራባዊ ባህልና በተሐድሶ አራማጆች ቤተ ክርስቲያኒቷን ለማደስ የሚደረገውን ጥረት ሁለቱንም የሚቃወምና ለዚህም እየሠራ ያለ አድኃሪ የሆነ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ ማኅበርም ቤተ ክርስቲያንን ለመለወጥ የሚደረገውን ማንኛውንም ነገር ለመከላከልና ለራሳቸው ማንነትና ኢትዮጵያ በዓለም ስላላት ቦታ አስፈላጊ ነው የሚሉትን የቤተ ክርስቲያኒቷን ገጽታ ለመጠበቅ ይፈልጋሉ፡፡”

http://www.Compassdirect.org/english/country.ethiopia/11092/ተሐድሶዎች ቤተክርስቲያናቸውን የሚወዱትንና ለእምነታቸውና ለሥርዓታቸው ተቆርቋሪ የሆኑትን ምእመናን፣ ካህናት፣ መነኮሳት … ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳን የሚባል ነገር መኖሩን ከነ ጭራሹ ያልሰሙ ሰዎች ቢሆኑም እንኳ “ማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ)” ናቸው የሚል ታርጋ በመለጠፍ ለማሸማቀቅ ይሞክራሉ፡፡ በዚህም የተሐድሶ ጉዳይ የሌለና የሆኑ ቡድኖች ጠብና ሽኩቻ ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ይጥራሉ፡፡ እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ለማመን የሚከብዱ የበሬ ወለደ ዓይነት የስም ማጥፋት ወሬዎችን በማኅበሩ ላይ በማሰራጨት ላይ ናቸው፡፡ ለምሳሌም በቅርቡ “የማኅበረ ቅዱሳን የሃያ አምስት ዓመት ስትራቴጂ ነው” በሚል ስም አንድን ሕፃን እንኳ ሊያሳምን በማይችል መልኩ ራሳቸው የፈጠሩትን አሉባልታ የማኅበሩ አስመስለው በሐሰት ማኅተም አትመው በኢንተርኔት አሰራጭተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የፈጠራ ክሶችንና ስም ማጥፋቶችን ደህና አድርገው ተያይዘዋቸዋል፡፡

ለ) የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደርና መዋቅር መቆጣጠር ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያኒቷን ለመለወጥና ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የተመቸች ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ ለመቆጣጠር የሚመኙት አንዱ ነገር የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደርና መዋቅር መያዝ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንደበት በመናገር፣ ቤተክርስቲያን ያልሆነችውን ናት፣ የሆነችውን ደግሞ አይደለችም በማለት ያሰቡትን የተሐድሶ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይረዳቸዋል፡፡


ወደዚህ ግብ ለመድረስም በተለያዩ ጊዜያትና ስልቶች ከመሪጌቶች፣ከቀሳውስት፣ ከመነኮሳት፣ ከዲያቆናትና ከሌሎችም መካከል በተለያየ ጥቅማ ጥቅምና ድለላ የማረኳቸውንና ያሰለጠኗቸውን ሰዎች በአስተዳደር መዋቅሩ ውስጥ ለማስገባትና ቦታውን ለመያዝ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የተወሰነ ርቀት መጓዝ ችለዋል፡፡ ይህም በስልታቸው እንደ ገለጹት “መንፈሳዊ ቀውስ የደረሰበትን አስተዳደር ማረምና ማስተካከል” (ኆኅተ ብርሃን፣ መጋቢት2000፣ ገጽ 16) በሚል ሽፋን የሚካሔድ ነው፡፡

ይህን ጉዳይ እስከ የት ድረስ መግፋትና ማድረስ እንደሚፈልጉ ሲገልጹም እንዲህ ብለዋል፡-
“ማቅ (ማኅበረ ቅዱሳን) ወደደም ጠላም ቤተ ክርስቲያኒቱ በእውነት በሚወዷትና የወንጌልን እውነት በሚያገለግሉ መምህራንና ሊቃውንት ይህንም እውነት ተቀብለው አምላካቸውን በንጹሕ ልብ ሆነው በሚያመልኩ፣ በተለይም መጪው ዘመን በትካሻቸው ላይ የወደቀባቸው ከመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን እየተመረቁ የሚወጡ የወንጌል አርበኞችና ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው አባቶች በሚወስዱት የማያዳግም እርምጃ ቤተ ክርስቲያናችን ተሐድሶን ታደርጋለች፡፡” (መጥቅእ፣ ኅዳር 2000፣ ገጽ 2) ጳጳሳት ሳይቀሩ የማያዳግም እርምጃ መውሰዳቸውና ቤተ ክርስቲያኒቱን ማደሳቸው የማይቀር መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም ይህን ሕልማቸውን እውን ለማድረግ የቤተ ክርስቲያኗን የአስተዳደር መዋቅር፣ እስከ ጵጵስና ደረጃ ያለውንም መቆጣጠር ዋና ስልታቸው ነው፡፡

ዛሬ የመነኮሱበት የማይታወቅ ሰዎች የአባቶቻችንን ቆብ አጥልቀው መስቀሉን ጨብጠው ቀሚሱን አጥልቀው ካባውን ደርበው፣ ያልሆኑትን መስለው፣ ሌሎችም የነበሩ፣ ዛሬ ግን ያልሆኑ፣ ዓላማቸውን እንደ ይሁዳ ለውጠው የክፋቱ ተባባሪ ሆነው ያሉ ሁሉ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ሲጫወቱ ዝም እየተባሉ ስለሆነ እነዚህ ሰዎች የነገዪቱ ጳጳሳት የማይሆኑበት እድል አይኖርም ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡

ይልቁንም አሁን ሃይማኖታቸው በግልጽ ፕሮቴስታንት (ተሐድሶ) የሆኑና ብዙ ጉድ ያለባቸው፣ የምግባር ድቀት ያንገላታቸው፣ የሃይማኖት አባት ሆነው ምእመናንን ለማስተ ማርና ለመምራት ቀርቶ ተነሳሒ ለመሆን እንኳ የከበዳቸው ሰዎች ዓይናቸውን በጨው ታጥበው ጵጵስና ለመሾም የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር አፋፍ ላይ እየደረሱ እየተ መለሱ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እንዲሁ ከቀጠለ እነዚህ ሰዎች አንድ ቀን የጳጳሳትን አስኬማ ደፍተው፣ በትረ ሙሴ ጨብጠው፣ “አቡነ” እገሌ ተብለው ላለመምጣታቸው ምን ዋስትና አለ? “ሞኝ ቢቃጡት የመቱት አይመስለውም” እንደሚባለው እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎችን ለጵጵስና እጩ አድርጎ እስከማቅረብ ደረጃስ እንዴት ሊደረስ ቻለ?


ማንነታቸው ተጣርቶ በንስሐ የሚመለሱት ቀኖና ሊሰጣቸው፣ የማይመለሱት ደግሞ ሊለዩ (ሊወገዙ) ሲገባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ሆነው በቤተ ክርስቲኒያቱ ህልውና ላይ ወሳኝ አካላት ሊሆኑ መታሰቡ በራሱ የሚያሳየው ከባድ ነገር አለ፡፡

እነዚህን ሰዎች በአድባራትና በገዳማት ዕልቅናና በተለያየ ሓላፊነት ከመሾም ጀምሮ ግልጽ የሆነ የአደባባይ ጉዳቸውን ዝም ከማለትና አልፎ አልፎም ከማበረታታት ጀምሮ በቤተ ክርስቲኒያቱ አስተዳደር ውስጥ እንዳሻቸው እንዲናኙበት የሚፈቅድና የሚመች የተሐድሶ ሰንሰለት አለማለት ይሆን?

እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆችና አባቶች እንደ እንጀራ ልጆች እየተቆጠሩና እየተገፉ እነዚህ ተሐድሶዎች ደግሞ ባለሟሎች መስለው ከዚያም አልፎ ለጵጵስና ታጭተው ማየትና መስማት በእጅጉ ያማል፣ ልብንም ያደማል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች አናት ላይ ወጥተው የጵጵስና መዓርግ ጨብጠው ከመጡ በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ሊያመጡ ያሰቡትን ስልታዊ አደጋ መገመት ውኃን የመጠጣት ያህል ቀላል ነው፡፡

ስለሆነም እነርሱ ያሰቡት ከባድ ትርምስ ሳይመጣ ‹ሳይቃጠል በቅጠል› እንዲሉ በጊዜ ከጸሎት ጀምሮ ማንኛውም ሊደረግ የሚገባውን የመከላከል ሥራ ከወዲሁ መፈጸም ይገባል፡፡ ቁጭ ብሎ የሰቀሉትን ቆሞ ማውረድ ያቅታልና፡፡ ይህም “እነ እገሌ ምን እየሠሩ ነው?” በሚለው ያልጠቀመን ፈሊጥ ሳይሆን “እኔ ምን አደረግሁ?

አሁንስ ምን ማድረግ አለብኝ?” በሚል ሊሆን ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር በቤቱ የተሰገሰጉ ይሁዳዎችን የሚያጋልጥበትንና ከመንጋው የሚለይበትን ዘመን ያቅርብልን፣ አሜን፡፡

ሰኔ 11 ቀን 2003 ዓ.ም

/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ልዩ እትም ግንቦት፣ 2003 ዓ.ም/ eotc-mkidusan.org/site/

Monday, June 13, 2011

Wednesday, June 8, 2011

የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣን የማገድ ሙከራ አንድምታ

“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።” የማርቆስ ወንጌል 16፥15

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ በ ኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ በሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ከጳጉሜን 1985 ዓ. ም ጀምሮ ለ18ዓመታት በየወሩ አሁን ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ በመታተም የቤተክርስቲያንን ዜናዎችን፣ ትምህርተ ወንጌልን፣የአባቶችን ሕይወት፣ ከምዕመናን የሚነሱ መንፈሳዊ ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት፣ የገዳማት እና አድባራት እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤቶችን እንቅስቃሴ በመዘገብ ምዕመናን በማስተማር፣በማሳወቅ እና መንፈሳዊ ችግር/ፈተና ፈቺ በመሆን አገልግሎት ስትሰጥ የኖረች የቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ነች::