በኤፕሪል 25 2010 የዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል አስተዳደር ቦርድ መልአከ ሣህል አወቀን በውድቅት ሌሊት በፖሊስ አስገድዶ በማስፍረም በክህነት ከሚያገለግሉበት የሥራ ገበታቸው ላይ እዲሰናበቱ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህንኑ የግፍ አሠራር በመመልከት ቀሲስ መስፍንም ሕዝቡን በዓውደ ምህረት ተሰናብተው በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን በመልቀቅ መውጣታቸውም ይታቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ የአስተዳደር ቦርዱ የቀጠራቸው ኬጂ 9 ቦምብ ፈታሽ ፖሊሶች ወደ ቤተ መቅደሱ በድፍረት ከነጫማቸው በመግባት ምእመናን ከጸሎት ገበታ ላይ በኃይል በመጎተት ደብድበዋል፤ በካቴና ብረትም ጠፍረው በማሰርም አሰቃይተዋል፡፡ ይህም በቴሌቪዥን የታየ ፤ ዓለምን ያስደነቀና ያስቆጣ አስገራሚ ክስተት ብዙዎችን ከቤተክርስቲያኒቱ አሽሽቷል፤አንዳንዶቹንም ሃይሞኖታቸውን እንዲቀይሩ አድርጓል፤ በርካታ የቤተክርስቲኒቱ ምእመናንም በመተባበር ድርጊቱንና አምባገነናዊውን የቦርድ አስተዳደርን በሕግ በመቃወም ጉዳዩን ፍርድ ቤት እንዲመለከተው አድርገዋል፡፡